የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጆሀንስበርግ እና ኬፕታውን ከተሞች ዳግም በረራ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጆሀንስበርግ እና ኬፕታውን ከተሞች ዳግም በረራ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ እና ኬፕታውን ከተሞች ዳግም በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።
የዓለም አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአየር በረራ መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ የጉዞ እገዳዎችን እንደጣሉ ይታወቃል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ አገራት ከተሞች የሚያደርገውን በረራ አቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የጉዞ እገዳዎች እየላሉ በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የአብራሪዎችና የበረራ ባለሙያዎችን ጤንነትና ደህነንት መጠበቅ የሚያስችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ዳግም መጀመሩን ለኢዜአ ዛሬ በላከው መግለጫ አስታውሷል።
በዚሁ መሰረት ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ እና ኬፕታውን ከተሞች የንግድ በረራዎችን እንደሚጀምርም አየር መንገዱ ገልጿል።
አገራት የጉዞ እገዳቸውን እያላሉና ድንበራቸውን እየከፈቱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ የደንበኞችና የበረራ ባለሙያዎችን ደህንነት መጠበቅ ትኩረት ባደረገ መልኩ የዓለም አቀፍ በረራዎችን ቁጥር ለመጨመር ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።