ከቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ንግድ 870 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ከቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ንግድ 870 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ የቡና፣ ሻይና የቅመማ ቅመም ምርቶች 870 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
500 አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ መውሰዳቸውንም አስታውቋል።
በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 270 ሺህ 835 ቶን ቡና 854 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ለኢዜአ ገልጸዋል።
ከ2011 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀርም በመጠን ከ40 ሺህ ቶን በላይ፤ በገቢ ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ከቡና ጎን ለጎን 12 ሺህ ቶን የሚጠጋ የቅመማቅመም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 16 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ገቢ መገኘቱም ተገልጿል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሪፎርም አሰራር መተግበር ከጀመረበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለይ የቡና ምርት መጠንና ጥራት ዕድገት ማሳየቱን አቶ ሻፊ ገልጸዋል።
በሪፎርሙ ቀደም ሲል የነበሩ ረጃጅም የቡና ግብይት ሰንሰለቶች ተወግደው የተለያዩ አሰራሮች መተግበራቸው ለቡና ገቢ መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አክለዋል።
በሌላ በኩል በሕገወጥ ደላሎች ሳቢያ የሚገባቸውን ዋጋ ሳያገኙ ይቀሩ የነበሩ አርሶ አደሮች በአዳዲሶቹ አሰራሮች መተግበር ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።
ከአዲሶቹ አሰራሮች መካከል አርሶ አደሩ ቡናውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብበት አሰራር መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ይህን ተከትሎም 500 አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተመዘግበው ፈቃድ መውሰዳቸውን አክለዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቡና ውድድር /ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ/ የተሳተፉ አርሶ አደሮች አንድ ኪሎ ቡና እስከ 13 ሺህ ብር ድረስ መሸጥ እንደቻሉም አስታውሰዋል።
አቶ ሻፊ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ቡና 87 በመቶው የጥራት ደረጃው ከፍተኛ እንደነበረ አውስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 312 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገኘት ታቅዷል ነው ያሉት።