ቀጥታ፡

የሁለቱ አገር መሪዎች የገቡትን ቃል በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ማድረጋቸው ለፍቅርና ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል

አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች  የገቡትን ቃል  በአጭር ጊዜ ተግባራዊ  ማድረጋቸው ለፍቅርና ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን በአዋሳ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ። “ግንኙነቱ የሁለቱ  አገሮች ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች ፍቅርን ዳግም የሚያረጋግጥ  ነው'' ብለዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና  የኤርትራ ህዝብ  ለጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አብይ  አህመድ ያደረጉትን አቀባበል  አድንቀው  የኢትዮጵያ ህዝብ በዛሬው እለት ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያደረገው አቀባበልም የሚመሰገን እንደሆነ ገልጸዋል። የአዋሳ ህዝብም ፕሬዚዳንቱን ለመቀበል መዘጋጀቱንና  በታሪካዊ ግንኙነቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ  የዛሬው ታሪካዊ ግንኙነት  የሁለቱን  ሀገራት የጋብቻና የቤተሰብ  ቅልቅል  ነው  ሲሉም ገልጸዋል። የአገር ሽማግሌው አቶ ደስታ ረኪሶ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ በመግባታቸው በጣም ነው ደስ ያለን ሰርጉ ሳምንት ነበር ያለፈው ዛሬ የቤተሰብ ቅልቅል ነው ብለዋል የሃዋሳ ከተማ ህዝብም በእልልታና በደስታ ለመቀበል ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡ ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ አረገታ ሪቄ በበኩላቸው የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረው በሁለቱ ሀገራት ሰላም ማስፈን የተራራቁ ቤተሰቦችን ማገናኘት ነው ብለዋል፡፡ አቶ አብርሃም አመኑ የተባሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በናፍቆት ሲጠብቁት የነበረ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም