ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሕግ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት የሚያስችል የሦስትዮሽ ሥምምነት ተፈረመ።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የፌዴራል የፍትሕ የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ጀስቲስ ፎር ኦል ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት ናቸው።

መዝገበ ቃላቱን ለማዘጋጀት በዓመት አራት ሚሊዮን ብር፤ ለማጠናቀቅ ደግሞ በአጠቃላይ 10 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የሚዘጋጀው መዝገበ ቃላት በአማርኛ ቋንቋ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች የሚዘጋጅ መሆኑም ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ እስካሁን የሕግ መዝገበ ቃላት እንዳልነበረ የተገለጸ ሲሆን አዲሱ መዝገበ ቃላት የሕግና ፍትህ ጽንሰ ሀሳቦችን ለሚገለገልበት ማኅበረሰብ በሚረዳው መልኩ ለማቅረብ እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

በሚኒስትር ማዕረግ የፌዴራል የፍትሕና የሕግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፣ እስካሁን በኢትዮጵያ በዘርፉ ምንም ዓይነት መዝገበ ቃላት ያለመኖሩን ገልጸዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ኢንስቲትዩቱ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ይሄን እውን ማድረግ የሚያስችል ሥምምነት ዛሬ መካሄዱን ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ይህ ሥራ በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ አማካኝነት የሚዘጋጅ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የሚዘጋጀው መዝገበ ቃላት የሕግና ፍትህ  ጽንስ ሀሳቦችን ለተገልጋዮች በማድረስ  ሁሉም እኩል አረዳድ እንዲኖረው በማድረግ በሕግ ሥርዓቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዚን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ ደግሞ የፍትህ አገልግሎቱ ተገማችና ወጥ ለማድረግ እንዲሁም አስቸጋሪ ቃላትን በተቀራረበ መንገድ ለመረዳት ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች ለማዘጋጀትም እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በመዝገበ ቃላቱ ላይ 4 ሺህ 500 ያህል ቃላትን ለመተርጎም እንደታቀደም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም