ቀጥታ፡

ለ350 አካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ ተደረገ

ሐረር ፣ መስከረም 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለሚገኙ 350 አካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው ኤስ.አይ.ዲ የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ከጀርመኑ ኮንቮይ ኦፍ ሆፕ ከተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።

ትናንት በተካሄደው የድጋፍ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችና ምቹ ያልሆኑ አካባቢዎች ያልተፈቱ የአካል ጉዳተኞች ችግሮች ናቸው።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ችግሮቹን ለመፍታት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለአካል ጉዳተኞች ለተደረገው የዊልቸር ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

የኤስ.አይ.ዲ ሥራአስኪያጅ አቶ ሰላምይሁን አክሊሉ ከጀርመኑ ኮንቮይ ኦፍ ሆፕ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በክልሉ ከ350 በላይ ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የዊልቸርና ሌሎች ቁሳቁሶች ደጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ የዊልቸር ድጋፉ መደረጉን አመልክተዋል።

ድጋፍ የተደረጉት ዊልቸሮች ሦስት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ምሥራቅ እሸቴ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለማቃለል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች መካከል ወይዘሮ ራሄል መላኩ ቀደም ሲል ይገለገሉበት የነበረው ዊልቸር በመበላሸቱ ተቸግረው መቆየታቸውን በማስታወስ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

ከዚህ ቀደም የዊልቸር ተጠቃሚ አልነበርኩም፤ የተደረገልኝ ድጋፍ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ያግዘኛል ብዬ አስባለሁ"ያሉት ደግሞ ሌላው አካል ጉዳተኛ አቶ መቻል ምሥጋናው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም