የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴው ምክረ ሀሳቦችን እንዲያቀርብ ተወሰነ

69

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ ምክረ ሃሳቦችን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብለት ወሰነ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ውላቸው በማለቁ ፌዴሬሽኑ ውላቸውን አለማራዘሙ ይታወቃል።

ፌዴሬሽኑ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች መቼ እንደሚደረጉ ባለመታወቁ የአሰልጣኙን ውል አለማራዘሙን መግለጹም የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከ20 እና 17 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችም በዚሁ ምክንያት ከስራ መልቀቃቸው ይታወቃል።

ይሁንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የአፍሪካና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች በህዳር 2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን ጉዳይ በተመለከተ ነው።

ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ዙሪያ አሉኝ የሚላቸውን ምክረ ሀሳቦች አዘጋጅቶ ለስራ አስፈጻሚው እንዲያቀርብ ወስኗል።

የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የሚቀርቡለትን ምክረ ሀሳቦች ተመልክቶ በቀጣይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2021 በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫና በኳታር እ.አ.አ በ2022 በሚካሄደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዞን በሚያካሄዳቸው ውድድሮች የኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ብሔራዊ ቡድኖች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዞን ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ወስኗል።

ብሔራዊ ቡድኖቹ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤት (ሴካፋ) በሚያወጣቸው መርሃ ግብሮች አማካኝነት ተሳታፊ ይሆናሉ።

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድንም በ2013 ዓ.ም በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር እንዲሳተፍ ተወስኗል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ መድህን ግብ ጠባቂ የነበረው ይልማ ከበደ (ጃሬ) በደረሰበት ህመም መንቀሳቀስ የማይችል (ፓራላይዝድ) በመሆኑ ለህክምና እንዲረዳው የ50 ሺህ ብር ድጋፍ እንዲደረግለት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል።

የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የፌዴሬሽኑ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሆነው እንዲሰሩ ወስኗል።

የዳይሬክተሩ ስራ አፈጻጸም እየተገመገመ ለስራ አስፈጸሚው ኮሚቴ እንደሚቀርብም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም