ቀጥታ፡

ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ፈርስት ኮንሰልት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ፈርስት ኮንሰልት የተባለ ተቋም በሰባት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኛ አቅርቦትን ዲጂታላዝድ ለማድረግ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አደረጉ።

ስምምነቱ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ላይ በማተኮር በፈርስት ኮንሰልት በኩል በሚተገብረው ብሪጅስ የተሰኘ መርሃ ግብር አማካኝነት የሚፈጸም ነው።

መሰረታዊ ክህሎት ያላቸው ሰራተኞችን ለኢንቨስተሮች ለማቅረብ፣ የሰራተኞችን መረጃ በዘመናዊ አሰረር ማደራጀት፣ ተወዳዳሪነትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የተደረገ ስምምነት ነው።

ደብረብርሃን፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ መቀሌና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሰራሩ ተግባራዊ የሚደረግባቸው እንደሆኑም ተገልጿል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ እንዳሉት ቀደም ሲል በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመሳሳይ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

መሰረታዊ ክህሎት ያላቸው ሰራተኞችን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማቅረብ አሰራሩን ወደ 7 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማስፋት እንዳስፈለገም አብራርተዋል።

በስምምነቱ መሰረት መርሃ ግብሩ ሰራተኞችን ምርታማ እንዲሆኑና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል። 

ኢንቨስተሮች በሰራተኛ ክህሎት ክፍተት ምክንያት የሚያነሷቸውን የምርታማነትና የጥራት መጓደል ጥያቄዎችም ለመፍታት ያግዛል ነው ያሉት።

ሌላው የዳታ ቤስ አሰራር በመርሃ ግብሩ የሚተገበር ሲሆን በፓርኮች የሚገኙ የሰራተኞችን ብዛት፣ ስልጠና የወሰዱና ያልወሰዱ፣ የለቀቁና አጠቃላይ የተደራጀ የሰራተኞች መረጃ እንዲኖር ይደረጋል።

መርሃ ግብር ለቀጣዮቹ አምስት አመታት ይዘልቃልም ተብሏል።

የብሪጅስ መርሃ ግብር ቡድን መሪ አቶ ሚካኤል አዲሱ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተወዳዳሪነት በመጨመርና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

የኢንቨስትመንትን ተወዳዳሪነት እየጎተቱ የሚገኙ የሰው ሃይል ብቃት፣ መረጃና ምርታማ ሰራተኞችን በወቅቱ አለማቅረብ የሚታዩ ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

የአሁኑ መርሃ ግብር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ወጣቶች በኢንዱስትሪ ፓርክ ሲቀጠሩ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ አውቀው እንዲመጡ ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይ በሚሰጡ የክህሎት ስልጠናዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ይሳተፋሉ ተብሏል።

መረሃ ግብሩ በ7 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያመጣው ውጤት ታይቶ በሌሎች የመንግስትና የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በቀጣይነት ተግበራዊ ይሆናል ተብሏል።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሸነር ለሊሴ ነሜ እና የብሪጅስ መርሃ ግብር ቡድን መሪ አቶ ሚካኤል አዲሱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም