የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባራት ውጤታማ ነበሩ - የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ - ኢዜአ አማርኛ
የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባራት ውጤታማ ነበሩ - የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ በ2012 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ተብለው ሊጠቀሱ እንደሚችሉ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለፀ።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ለኢዜአ እንዳሉት የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ተቋሙ ብዙ ርቀት የሔደበት ነው።
ወቅቱ ሁከትና ብጥብጥ የተከሰተበት፤ ሕይወትና ንብረት የጠፋበት ሲሆን ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ ውጤታማ ተግባራት የተመዘገቡበት ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ክርክር በተጀመረባቸውና ክስ በተመሰረተባቸው ጉዳዮች መጓተት መፈጠሩን ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመት ችግሮቹን ለመፍታትና የተቋሙን የሰው ኃይል ለማጎልበት ይሰራል ብለዋል።
የተጀመሩ የሕግ ማስከበር ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችሉ አካሔዶችን በመቀየስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።
ዶክተር ጌዲዮን የዘንድሮ የተቋሙ ዋነኛ ተግባር ባለሙያው ብቃቱን እንዲያሳድግና ሙያዊ ስነ-ምግባሩን እንዲያጎለበት ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።
የመረጃ አያያዝና ተደራሽነት ስራዎችን በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጡ ፍጥነትና ጥራት እንዲኖረው የሚያደርጉ እቅዶች እንደሚተገበሩም ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ አቶ ፈቃዱ ፀጋዬ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ ያከናወነው የሕግ ማርቀቅ ተግባር በስኬት ከሚጠቀሱ ስራዎቹ መካከል ናቸው ይላሉ።
የተቋሙን ስራዎች ለማሳደግና ለአገልግሎት ፈላጊ አካላት የተሻለ ምላሽ ለመስጠት ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ መደረጉንም ገልጸዋል።