ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር 280 መኖሪያ ቤቶችን ሊገነባ ነው

ጎንደር ኢዜአ መስከረም 11/2013 በማእከላዊና ምእራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረ ግጭት መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አርሶ አደሮች በ24 ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታወቀ።

ማህበሩ በሁለቱ ዞኖች የሚገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች ማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጎንደር ከተማ ከአጋር አካላት ጋር የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

የማህበሩ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ እንግዳ ማንደፍሮ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት ማህበሩ በአዲሱ አመት 280 መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅቱን አጠናቋል።፡

መኖሪያቸው ከተቃጠለባቸው አርሶ አደሮች በተጨማሪ አቅመ ደካሞች፣ ደጋፊ የሌላቸው ሴቶችና አካል ጉዳተኞችም የመኖሪያ ቤት ግንባታው ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል። 

ማህበሩ የሚገነባቸው መኖሪያ ቤቶች የግል መፀዳጃ ቤት ጭምር እንደሚኖራቸው ጠቁመው፤ ህብረተሰቡም በጉልበትና በቁሳቁስ ጭምር አስተዋጽኦ በማድረግ የሚሳተፍበት እንደሆነ አስረድተዋል።

“ማህበሩ የቤቶቹን ግንባታ ከመጭው ጥቅምት ወር 2013 ዓ/ም በማስጀመር በዓመቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ነዋሪዎቹ እንዲረከቡ ይደረጋል”ብለዋል። 

በተጨማሪም በሁለቱ ዞኖችና በምእራብ ትግራይ ሁለት ወረዳዎች የህብረተሰቡን የግልና የአካባቢ ንጽህና ለመጠበቅ የሚያግዝ የጤና አጠባበቅ ፕሮጀክት እንደሚተገብርም ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚውለውን በጀትም ማህበሩ ከአሜሪካን አለምአቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስ አይ ዲ/ በድጋፍ እንዳገኘም አስታውቀዋል፡፡ 

የማእከላዊ የሰሜንና የምእራብ ጎንደር ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ሃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ በበኩላቸው ማህበሩ ባለፈው አመት በማእከላዊና ምአራብ ጎንደር ዞኖች ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ወገኖች 120 መኖሪያ ቤቶችን ሰርቶ አስረክቧል።

በዞኑ በግጭት ሳቢያ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ወገኖች በክልሉ መንግስት ድጋፍና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ3 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል ያሉት ደግሞ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባንቲሁን መኮነን ናቸው።

ዘንድሮም ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ700 በላይ ቤቶች ለመገንባት አቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው “አስተዳድሩ ቀይ መስቀል ለሚያስገነባቸው ቤቶች አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል”ብለዋል። 

ከምእራብ ጎንደር ዞን የመጡት አርሶ አደር አያል ዘገየ በበኩላቸው አምና በዞናቸው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በቀበሌአቸው የተቃጠሉ 475 ቤቶች እስከ አሁን አለመሰራታቸውንና በአንድ ቤት በርካታ ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ቀይ መስቀል ከሰብአዊ እርዳታ ባሻገር ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ወገኖች እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው” ያሉት አርሶ አደሩ ዘንድሮም በመተሳሳይ ቤት ለመገንባት መዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን በ2012 ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ከ58 ሺህ በላይ አባወራዎችና እማወራዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ከዞኑ አስተዳድር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም