ቀጥታ፡

በተያዘው የመስከረም ወር ስድስት የድንበር ኬላዎች ይከፈታሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ ስድስት የድንበር ኬላዎችን እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ እንደምትከፍት የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ኡበቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ካላት የድንበር ስፋት አንጻር አሁን ያሏትን 12 የድንበር ኬላዎች ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል።

በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ከተለያዩ የውጭ አገሮች ድንበሮችን አቋርጠው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትን ለመቆጣጠር የድንበር ኬላዎች እንዲከፈቱ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ኤጀንሲው ከክልሎች ጋር በመሆን የድንበር ኬላዎችን በጥናት ለመክፈት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጥናት ከተለዩ የድንበር ኬላዎች ውስጥ ስድስቱ እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ሙሉ ለሙሉ የሚከፈቱ ሲሆን ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር አንዳንዶቹ በይፋ ባይመረቁም በአሁኑ ወቅት ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኬላዎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው።

የሚከፈቱት ስድስቱ የድንበር ኬላዎች በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ክልሎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በኮቪድ -19 ምክንያት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር ሲባል ኬላዎቹ በይፋ እስኪከፈቱ ድረስ የተወሰኑት የሰው ኃይል ተመድቦላቸው አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩም አቶ ታምሩ ተናግረዋል።

ለኬላዎቹ አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት እስከ መስከረም 30ቀን 2013ዓ.ም ድረስ ስድስቱም ኬላዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ድንበሮች መከፈታቸው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ ሰዎችን በመቆጣጠር የአገርን ደህንነት ለመጠበቅ ያስችላል።

"በተጨማሪም ድንበር በሚጋሩ ሁለት አገሮች መካከል የዲፕሎማሲና ሌሎች ግንኙነቶች እንዲጠናከር በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ድንበሮች ሲከፈቱ የንግድ ልውውጥና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች እንደሚጠናከሩም  ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም