ቀጥታ፡

በፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ12 ሺህ ዩሮ በላይ ገንዘብ ለሕዳሴው ግድብ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከትናንት በስቲያ በአካልና በዙም መተግበሪያ ተካሄዷል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ ላይ በፈረንሳይ፣ በስፔንና በፖርቹጋል የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መሳተፋቸው ተገልጿል።

በመርሃግብሩ በሦስቱ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከ12 ሺህ በላይ ዩሮ መሰብሰቡን በፈረንሳይ፣ በስፔንና ፖርቹጋል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ መግለጻቸውን በፓሪስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደሩ በፈረንሳይ ለሚገኙ የሕዳሴ ግድብ የድጋፍ ኮሚቴ አባላት እና በፈረንሳይ፣ በስፔን እና በፖርቱጋል ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ በገንዘብ መዋጮ፣ በሙያ እንዲሁም የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት የሚደረገውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚቻል ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ገንቢ የሀሳብ ልውውጥ መደረጉንም አምባሳደር ሄኖክ አመልክተዋል።

የድጋፍ ማሰባሰቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አምባሳደር ሄኖክ፣ ለሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር በ2013 ዓ.ም በፈረንሳይ፣ ስፔን እና ፖርቱጋል ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል።

"በአንድነት ቆመን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተሳካ ሁኔታ እናጠናቅቃለን" ብለዋል አምባሳደር ሄኖክ በዝግጅቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት።

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ስራዎች የሚሸፍን ነው።

የፈረንሳይና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ማህበር ከሊዮን ሜትሮፖል ከተማ ጋር በመተባበር ግምታቸው ከ35 ሺህ 500 ዩሮ በላይ የሆነ የሕክምና ቁሶችና መሳሪያዎችን ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ማሰባሰቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም