የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነ-ስርዓት ተፈጸመ
ሰመራ መስከረም 11/ 2013 (ኢዜአ)የአፋር መንፈሳዊ መሪ ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ በአይሳኢታ ከተማ ተፈጸመ።
የቀብር ስነ-ስርዓቱ ከመፈጸሙ በፊት የስንብት መረሃ ግብር ተካሄዷል።
ሱልጣን ሃንፍሬ ሃንፈሬ አሊሚራ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል በአይሳኢታ ከተማ ፣ከአምስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል በአስመራ ፣ ከሰባተኛ እስከ 12 ክፍል ደግሞ በአዲስ አበባና ካይሮ ግብጽ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን በቀብር ስነ-ስርዓቱ ወቅት በተነበበው የህይወት ታሪካቸው ተገልጿል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፖለቲካል ሳይንስ ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ዩኒቨርሲቲ አገኝተዋል።
ሱልጣን ሃንፈሬ በህይወት ዘመናቸው የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድርና በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ደግሞ በዕርቀ ሠላም ኮሚሽን አባልነት ሲያገለግሉ እንደነበር ከህይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።
በቀብር ስነ - ስርዓታቸው የጁቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ በኤርትራ እና ጁቡቲ የሚገኙ የአፋር ሱልጣኖች ፣ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የሠላም ሚኒስትር ፣ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዎሪዎች ተገኝተዋል።
ሱልጣን ሃንፈሬ አሊሚራ የአምስት ሴት እና ሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።
ሱልጣኑ ባደረባቸው ህመም በአዲስ አበባ የህክምና እርዳታ ሲደርግላቸው ቆጥቶ በተወለዱ በ74 ዓመታቸው ከትናንት በሰቲያ ከዚህ ዓመት በሞት መለያታቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።