የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከልና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከልና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ)የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል እና የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ተዛማጅ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ፤ ማዕከሉ በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የተቋቋመ መሆኑን አብራርተዋል።
በአገሪቱ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተው የሚገኙ ግለሰቦችን የመከታተልና መቆጣጠር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ማዕከሉ የታክስ ስወራ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሌሎች ተዛማጅ ወንጀሎችን ተከታትሎ ለፌዴራል ፖሊስ ማስተላለፉን አስታውሰዋል።
በመሆኑም አሁን የተደረሰው ስምምነት የማእከሉን ስራ የሚያጠናክር መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ በማስመሰል ወደ ፋይናንስ ስርዓቱ እንዳይቀላቀል በጋራ የሚሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላ እንደገለጹትም ስምምነቱ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ወደ ተቋማት እንዳይገባ በጋራ ለመስራት ያግዛል።
ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ በመረጃ ልውውጥ፣ በሙያዊ አቅም ግንባታና ወንጀልን በጋራ በመከላከል ላይ የሚያተኩር መሆኑም ታውቋል።
በአፍሪካ በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል ስጋቶች ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ መሆኑ ይነገራል።
በአውሮፓዊያኑ 2019 የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከአህጉሪቱ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ስጋት ላይ ከወደቁ አገራት መካከል ሞዛምቢክ በግንባር ቀደምትነት ተቀምጣለች።
በ2020 በምስራቅ አፍሪካ ኬንያ በአምስት የተለያዩ ባንኮቿ 385 ሚሊዮን ሽልንግ ወይም 3 ነጥብ 75 ሚሊዮን ዶላር በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ እንደተገኘም መረጃዎች አመላክተዋል።