ዩጋንዳ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለስድስት ወራት የዘጋችውን ድንበርና ኤርፖርቷን ከፈተች - ኢዜአ አማርኛ
ዩጋንዳ በኮቪድ-19 ሳቢያ ለስድስት ወራት የዘጋችውን ድንበርና ኤርፖርቷን ከፈተች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) ዩጋንዳ በኮቪድ-19 ሳቢያ ላለፉት ስድስት ወራት ዝግ ሆነው የቆዩትን ድንበሯንና ኤርፖርቷን ክፍት አደረገች።
ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ባለፈው ቅዳሜ ባስተላለፉት መልዕክት አገሪቷ ድንበሯንና ኤርፖርቷን ክፍት ማድረጓን ይፋ አድርገዋል።
በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ላለፉት ስድስት ወራት ተዘግቶ የቆየው እንቅስቃሴ ዳግም ክፍት ተደርጓል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሚደረገው ጥንቃቄ ግን ይቀጥላል ብለዋል።
የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመግታት መንግስት የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ወደ ዩጋንዳ የሚመጣ የየትኛውም አገር ዜጋ የምርመራ ውጤቱ ከ72 ሠዓታት ያላለፈ ከኮሮናቫይረስ ነፃ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መያዝ ይኖርበታልም ብለዋል።
የምርመራ ውጤቱ ተቀባይነት የሚኖረው በየአገራቱ ከሚታወቁ ሕጋዊ ላቦራቶሪዎች ብቻ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
እንደ ሙሴቬኒ ገለጻ ከሆነ ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ ሳምንት በከፊል ይከፈታሉ፤ የአምልኮ ስፍራዎችም በጥብቅ ጥንቃቄ አማኞቻቸው የሚገለገሉባቸው ይሆናሉ።
የዩጋንዳ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአገሪቷ ኤርፖርት ለበረራ አገልግሎት ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል ሲልም አናዶሉ ዘግቧል።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ ጨምሮ ሌሎች አየር መንገዶች በረራቸውን ዳግም እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።
የዩጋንዳ፣ የቱርክ፣ የኳታር፣ የኬንያና የኤምሬቶችን ጨምሮ የተለያዩ አገራት አየር መንገዶች በረራቸውን ዳግም እንደሚጀምሩም አረጋግጠዋል።
የኢንተቤው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከካርጎ አገልግሎት በቀር ላለፉት ስድስት ወራት የማጓጓዝ አገልግሎቱን አቋርጦ ቆይቷል።
በዩጋንዳ እስካሁን 6 ሺህ 287 የአገሪቷ ዜጎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ 63 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነው ኮቪድ-19 በተለይ በቱሪዝምና አቪዬሽን ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩ ይታወቃል።