የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አስክሬን ሰመራ ከተማ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አስክሬን ሰመራ ከተማ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት
ሰመራ መስከረም 11/2013 (ኢዜአ) የአፋር መንፈሳዊ መሪ የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አስክሬን ዛሬ ሰመራ ከተማ ሲገባ አቀባበል ተደረገለት።
በአቀባበሉ ስነ-ስርዓት የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ፣ የኃይማኖች አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።
የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነ-ስርዓት በትውልድ ስፍራቸው አይሳኢታ ዛሬ እንደሚፈጸም ታውቋል።
በቀብሩ ስነ-ሰርዓት የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አካላት እንዲሁም የጅቡቲ መንግስት ተወካይ እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ሱልጣኑ ባደረባቸው ህመም በአዲስ አበባ የህክምና እርዳታ ሲደርግላቸው ቆይቶ በተወለዱ በ74 ዓመታቸው ከትናንት በሰቲያ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ በሃገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ በስደት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።
በውጭ ቆይታቸው ለአፋር ሕዝብ በጥቅል ለኢትዮጵያዊያን መብት ሲታገሉና ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለውጡን ለማስቀጠል ከህዝባቸው ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ከ2004 ጀምሮ ህዝባቸውን በመንፈሳዊ መሪነታቸው ያገለገሉ ሲሆን በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም አገልግለዋል።