ድጋፉ 'የአብሮነታችንና አንድነታችን' ማሳያ ነው---ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ድጋፉ 'የአብሮነታችንና አንድነታችን' ማሳያ ነው---ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተደረገው ድጋፍ 'የአብሮነታችንና የአንድነታችን' ማሳያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
''ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አፋር መኖሩን አረጋግጠናል'' ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አድርጓል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በአስተዳደሩና በአዲስ አበባ ወጣቶች የተሰበሰበውን 12 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስና ገንዘብ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።
በክልሉ የአዋሽ ወንዝ መሙላት ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ከሞቀ ቤታቸውና ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 144 ሺህ ይደርሳል።
አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብና በዘላቂነት ለማቋቋም 350 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት፤ በክልሉ የደረሰው የዜጎች መፈናቀል አሳዛኝ ቢሆንም የሰው ሕይወት አለመጥፋቱ መልካም ነው።
ንብረት በጋራ ተሠርቶ የሚተካ መሆኑን ገልጸው፤ ''ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ለአብሮነታቸን ማሣያ እንጂ በቂ አይደለም'' ብለዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአፋር ተፈናቃዮች የሚያደርገው ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው አመልክተዋል።
"እኛ ከአሁን በፊት በአካል መጥተን ባንጠይቃችሁም በመንፈስ አብረን ነበርን" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ''አብሮነታችን በጋራ በመልማትም ይቀጥላል'' ብለዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ክልሉ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ በበረሃ አንበጣና በጎርፍ አደጋ እየተፈተነ መሆኑን ገልጸዋል።
''ይሁን እንጂ ከሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ የሚታየው አብሮነትና የሚደረገው ድጋፍ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አፋር መኖሩን አረጋግጠናል'' ብለዋል።
''በክልሉ የደረሰውን አደጋ ለመከላከል የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ከተባበርን የማንወጣው ችግር እንደማይኖር ማሣያ ነው'' ብለዋል
አያይዘውም ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የውስጥ ሰላም መፍጠር ከተቻለ "የድንበሩን ነገር ለእኛ ተዉት እኛ እንወጣዋለን" ብለዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም አዲስ አበባና ሠመራ በተለያዩ የልማት ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።