ቀጥታ፡

አራዳ ክፍለ ከተማ ለሕዳሴው ግድብ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2013 (ኢዜአ) አራዳ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድበ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀው ገንዘቡ የተሰበሰበው ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው እንቅስቃሴ ነው፡፡


የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ዛሬ በተካሄደው የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ላይ እንደገለጹት አራዳ ክፍለ ከተማ የግድቡን ዋንጫ ባለፈው ሳምንት ከልደታ ክፍለ ከተማ መረከቡን አስታውሰዋል።

በሐምሌና ነሐሴ ወራት እንዲሁም ዋንጫውን ከተረከበ በኋላ ባደረገው ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አግኝቷል፡፡


የአራዳ ክፍለ ከተማ በጥሬ ገንዘብ ካሰባሰበው ድጋፍ በተጨማሪ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገባቱንም ተናግረዋል።


በቀሪ ጊዜያት ተጨማሪ የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ከዕቅድ በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።


የዓባይ ወንዝ ፍትሀዊ አጠቃቀም ጥያቄ ለዘመናት ሲነሳ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ምስክር ግድቡን በስኬት ለማጠናቀቅ ህዝብን በማሳተፍ እየተሰራ ያለው ሥራ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።


ባለፈው ዓመት ማጠናቀቂያ በግድቡ የመጀመሪ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፣ በተያዘው ዓመት የግድቡ ሁለት ተርባይነሮች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አመልክተዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ የአራዳ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ በበኩላቸው፣ ህብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ ያደረገው አስተዋጽኦ እንደሚያኮራ ተናግረዋል፡፡


አራዳ ክፍለ ከተማ በኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የሚበዛበት ቢሆንም በጥቂት ወራት ብቻ በበጀት ዓመቱ ለህዳሴው ግድብ ለመሰብሰብ ከታቀደው 70 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ለማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል።


"ይህም የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለአገራዊ እድገቱ ያላቸውን ፍላጎት ያሳየ ነው" ብለዋል፡፡

በቀጣይ የሚከበሩት የመስቀል እና የእሬቻ ህዝባዊ የአደባባይ በዓላት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተከብረው እንዲጠናቀቁ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


የአራዳ ክፍለ ከተማ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀሐዬ በኩረጽዮን በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ ለሕዳሴው ግድብ 70 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ ወድስራ መገባቱን አስታውሰዋል።


ይሁንና ባለፉት ሁለት ወራት እና የሕዳሴው ዋንጫ ወደ ክፍለከተማው መግባቱን ተከትሎ በአምስት ቀናት ውስጥ በተደረገ የህዝብ ንቅናቄ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተሰበሰበው እና ቃል ከተገባው በድምሩ ከ75 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡


የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ክፍለ ከተማው ከ96 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት አሰባስቦ ገቢ ማድረጉንም አቶ ጸሐዬ አመልክተዋል፡፡

ዛሬ በተካሄደው የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ላይ አራዳ ክፍለ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ የተረከበውን የህዳሴ ዋንጫ ለወረዳ 3 አስረክቧል፡፡

በቀጣይም ዋንጫው በአራዳ ክፍለ ከተማው በሚገኙ አሥሩም ወረዳዎች እየተዘዋወረ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ታውቋል።


በሥነ ስርዓቱ ላይ በክፍለ ከተማው የሚገኙ የአሥሩ ወረዳዎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በመድረኩም የተለያዩ ኪነጥበባዊና ባህላዊ ዝግጅቶች ለታዳሚው ቀርበዋል፡፡ (ኢዘአ) 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም