ሰላም ለሁሉም የአብሮነት መሰረት በመሆኑ ሰላምን በጋራ መጠበቅ ይገባል --- የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ሰላም ለሁሉም የአብሮነት መሰረት በመሆኑ ሰላምን በጋራ መጠበቅ ይገባል --- የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2013(ኢዜአ) ሰላም ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች የአብሮነትና የአንድነት መሰረት በመሆኑ ሰላምን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በነገው ዕለት የሚከበረውን የዓለም የሰላም ቀን ምክንያት በማድረግ "አብሮነታችን ለሰላማችን" በሚል መሪቃል ዛሬ የሰላም የእግር ጉዞ ወሎ ሰፈር ከሚገኘው ቦሌ አደባባይ እስከ ጎርጎሪዮስ አደባባይ ተካሂዷል።
በእግር ጉዞ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ሠራተኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፏል።
"ሰላም የሁሉም ኢትዮጵያዊ የአብሮነትና አንድነት መሰረት በመሆኑ ሁላችንም ሰላማችንን በጋራ መጠበቅ አለብን" ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አልማዝ ተናግረዋል።
ሰለም ከአንድነትና ከአብሮነት ውጭ ትርጉም የሌለው ጉዳይ በመሆኑ ዜጎች ሰላም ከአብሮ መኖር ጋር የተሳሰረ ሲሆን የበለጠ ውጤት እንዳለው ተረድተው ለሰላማቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ አስገንዝበዋል።
"ሰላም ከውስጣችን ይጀምራል፤ በመሆኑም ከራሳችን ጋር ሰላም በማውረድ ከሌሎች ጋር ሰላም ማውረድ ያስፈልጋል" ያሉት ወይዘሮ አልማዝ፣ የሌሎች ሰላም ለራስ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የልጇቿን አንድነትና ህብረት በእጅጉ እንደምትፈልግ ጠቁመው፣ ዛሬ የተካሄደው የእግር ጉዞ የመተባበር፣ የመተጋገዝና የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።
"በእግር ጉዘው ጤናችንን እየጠበቅን ለሁለንተናዊ ሰላማችን በፍቅር አብርን መጓዝ አለብን "ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የእግር ጎዞው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ያለ ሰላም መኖር እንደማይቻልና ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከእግር ጉዞ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ህይወት ተመስገን "በመደማመጥ ሁላችንም ሰላማችንን መጠበቅ ይገባናል" ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች በሰከነ መንፈስ ተረጋግተው በመንቀሳቀስ የራሰቸውንና የህዝባቸውን ሰላም መጠበቅ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
አቶ ገረመው ቱሉ በበኩላቸው "አገሪቱን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም በመተባበርና በአንድነት ሰላሙን መጠበቅ ይኖርበታል" ብለዋል።
"በተለይ አዲሱ ትውልድ የአባቶቹን ምክር መሰማት አለበት፤ በፍቅርና በአንድነት አብሮ መኖርን ከአባቶቹ ሊማርም ይገባል" ብለዋል።