ቀጥታ፡

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያ ጉብኝት በዓለም መገናኛ ብዙሃን እይታ

ምህረት አንዱአለም /ኢዜአ/:-   በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ አዲስ አበባ መግባቱን ተከትሎ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ምን አሉ? የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ  ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዝዳንቱ እና የሚመሩት ልዑካን ቡድን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የተለያዩ ክልል መሪዎችና ባለስልጣናት የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ሮይተርስ የዜና ማዕከል ባወጣው ዘገባ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያና በኤርትራ የተጀመረውን የወዳጅነት ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ አበባ ገብተዋል በሏል። አዲስ አበባዎች የሁለቱን ሀገራት ሰንድቅ አላማ በማውለብለብ በዝማሬና በተለያዩ ስነስርዓቶች ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን አስነብቧል። አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሰንደቅ ዓላማ ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በያዙ በርካታ ሰዎች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በደህና መጣችሁ የሚሉ ባነሮችም በመዲናዋ ጎዳናዎች ተሰቅለው የሁለቱ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ሲውለበለቡ ነበር ብሏል፡፡ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ መምጣት የበርካቶችን ቀልብ የሳበው የሁለቱን ሀገራት ሰላማዊ ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ፎቶ ያለበት ቲ-ሸርት ለብሰው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ ባሉት ዋና ዋና መንገዶች አቀባበል ሲያደርጉ እንደነበርም አመላክቷል። ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 20 ዓመታት በመካከላቸው የነበረውን ጥል በሳምንታት ውስጥ በማስወገድ ወደ ሰላምና ወዳጅ ጎረቤትነት መጥተዋል ነው ያለው። ሮይተርስ ሁለቱ ሀገራት በ1990ዎቹ ባደረጉት ጦርነት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሶ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና ኤርትራ በአለመግባባት ላይ እንደነበሩ አንስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ወደ ስልጣን  ሲመጡ ከኤርትራ ጋር ያለው አለመግባባት እንዲወገድና ወደ ሰላምና ወዳጅነት እንድንመጣ እንፈልጋለን ያሉትን ጥሪም በዘገባው አካቷል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ በኤርትራ ተቀባይነት አግኝቶ ሁለቱ ሀገራት አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውን ዳሷል። የኢሳያስን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከዘገቡት የውጭ መገናኛ ብዙሃን ቢቢሲ አንዱ ነው። ቢቢሲ በዘገባው በ1990 ዓ.ም ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተካሄደው ጦርነት ካበቃና ሁለቱ ሃገራት ለ20 ዓመታት በፍጥጫ ውስጥ ከቆዩ በኋላ በመሪ ደረጃ ጉብኝት ሲደረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት የመጀመሪያው ነው ብሏል። የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ኢትዮጵያና ኤርትራ የተፈራረሙትን የሰላምና ወዳጅነት ግንኙነት በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ያለመ እንደሆነም  አትቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ወደ አስመራ ባቀኑበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር ባደረጉት ስምምነት ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንዲያድሱና በመካከላቸው ያለውን ጦርነት በይፋ ለማቆም መስማማታቸውን አስታውሷል። የንግድ ግንኙነት ለመጀመርና በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት መስማማታውም ይታወቃል። የፕረዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረግ በጠላትነት ይተያዩ የነበሩት ሀገራት ወደ እውነተኛ ሰላማዊ ግንኙነት መመለሳቸውን እንደሚያረጋግጥም አስነብቧል። ሁለቱ ሀገራት ለ20 ዓመታት ያህል በጠላትነት ሲተያዩ መቆየታቸው በአጠቃላይ በምስራቅ አፍርካን ቀጠና ላይ አሉታዊ ጫና እንደነበረው እና አሁን ሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ግንኙነት መጀመራቸውም ለቀጣናው መልካም ዜና መሆኑ በቢቢሲ ዘገባ ተካቷል። የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት በቀጣይ ምን ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል የሚለው የቢቢሲ ትንታኔ ጠቅላይ  ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአስመራ በፈረሙት ስምምነት መሰረት ሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያቸውን የማደስ ስራ ጀምረዋል ይላል። የትራንስፖርትና የስልክ ትስስሮች ስራ እንዲጀምሩ የተደረገ ሲሆን በሁለቱም ሀገራት የሚገኙ ቤተሰቦች በስልክ መገናኘት ችለዋል። ባለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል የቀጥታ ጉዞ ተከልክሎ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቀጣዩ ሳምንት ወደ አስመራ የቀጥታ በረራ ይጀምራል። ይህ ደግሞ በነበረው አለመግባባት ምክንያት በኢትዮጵያና በኤርትራ የሚገኙና ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች ተመልሰው እንዲዋሃዱ እድል ፈጥሯል። አሶሼትድ ፕሬስ ደግሞ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የግንኙነት ጅማሮ በአስደናቂነት እንዲቀጥል አድርጎታል በሚል ርዕስ ይዞ ወጥቷል። ኤርትራን ለረጅም ዓመታት በመምራት ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ በሽዎች የሚቆጠሩ የመዲናዋ ነዋሪዎች በጎዳናዎች ላይ ወጥተው አቀባበል ማድረጋቸውንም ጠቅሷል። የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አቀባበል በጥብቅ የፀጥታ እና ደህንነት አባላት የታጀበ እንደነበርም ነው የገለጸው። ጠቅላይ  ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም እና ወዳጅነት ግንኙነት እንዲጀምሩ በማድረግ የመጀመሪያውን ታሪክ ቢፅፉም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ግንኝነቱን በጠንካራ አለት ላይ  የተመሰረተ እንዲሆን አድርጓል ብሏል። አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባው ኢትዮጵያውያን በሰጡት አስተያየት በጠላትነት ሲፈራረጁ የነበሩት ሁለቱ ሀገራት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በመመለሳቸው መደሰታቸውን ጠቅሷል። የሁለቱ ሀገራት ከለየለት ጠላትነት ወደ ከፍተኛ ወዳጅነት መምጣትም በበርሊን የነበረው ግንብ ከተደረመሰበት ሁኔታ ጋር አነጻጽረው እንደሚመለከቱት ነው ያተተው። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታሪካዊውን ጉብኝት በኢትዮጵያ ማድረግ ጀምረዋል ያለው ደግሞ ፍራንስ 24 ነው። የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝትም ኢትዮጵያና ኤርትራ የነበራቸውን በጠላትነት የመተያየትና አለመተማመን አስወግደው የጀመሩትን አዲስ ግንኙነት እንደሚያጠናክርም ጠቁሟል። ሁለቱ ሀገራት የሰላምና ወዳጅነት ግንኙነት መጀመራቸውን ተከትሎም የኤርትራ ኤምባሲ በአዲስ አበባ እንደሚከፈት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ መናገራቸውን በዘገባው ይዞ ወጥቷል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት የሚመሩት ልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ መግባቱን በጠቀሰው ሀተታው፥ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘውን የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚጎበኙም አንስቷል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መጀመር በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በመሰረታዊነት እንደሚለውጠው ተመልክቷል። የለውጥ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር መልካም ግንኙነቷን የበለጠ እንድታጠናክር እየሰሩ መሆኑን አውስቷል። ሱዳን ትሪቢዩን ደግሞ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ግንኙነት መጀመር የሁለቱን ሀገራት የወዳጅነት ስምምነት በገቢራዊነት ደረጃ እንደሚያጠናክረው ነው ያስነበበው። ዋሽንግተን ፖስት ደግሞ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ ብሏል። የኢትዮጵያና የኤርትራ የወዳጅነት ግንኙነት መጀመርም ከተሾሙ 100 ቀናት ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የፈጠሩት የዲፕሎማሲያዊ የአስተሳሰብ ለውጥ መሆኑን ነው የተነተነው። ኢትዮጵያ በኤርተራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ የተባበሩት መንግስታትን መጠየቋም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ መልካም ሁኔታ መቀየሩን የሚያስረግጥ ሀቅ ነው ሲል ገልጾታል። አልጀዚራ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሶስት ቀናት ለሚያደርጉት ታሪካዊ ጉብኝት አዲስ አበባ መሆናቸውን በድረገፁ አስነብቧል። የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ያልተጠበቀ የሰላምና ወዳጅነት ግንኙነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ነው ያነሳው። በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበሩት ነባራዊ ሁኔታዎች በፍጥነት መለወጣቸውን በርካቶችም ይህን ፈጣን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በግርምት እየተመለከቱት ነው ብሏል። በነገው ዕለትም በሚሊኒየም አዳራሽ 25 ሺህ ሕዝብ የሚታደምበት ዝግጅት እንደሚካሄድና በዚሁ ስፍራ ሁለቱም መሪዎች ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ አስመራ በሄዱ በቀናት ልዩነት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውም የሀገራቱን የሰላምና ወዳጅነት ግንኙነት በፍጥነት ለመተግበር ያለውን ተነሳሽነት ያሳያል ሲሉ ፕሬስ ቲቪ፣ ቲ አር ቲ፣ ኒውዮርክ ታይምስ እና  ሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም