ቀጥታ፡

የመስቀል በዓል ኮቪድ-19 ለመከላከል ሲባል የተወሰኑ ምዕመናን በተገኙበት ይከበራል - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013(ኢዜአ) የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽ መከላከልን መሰረት አድርጎ የተወሰኑ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።

በመስቀል በዓል ዋዜማ የሚከበረው የደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በእምነቱ ተከታዮች በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው።


በዓሉ ቤተክርስቲያኒቷ ከምታከብራቸው ዘጠኝ የኢየሱስ ክርስቶስ ንዑሳን በዓላትም አንዱ እንደሆነም የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ።


ደመራ የሚለው ቃል ደመረ፣ ጨመረና አንድ አደረገ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰባሰብን፣ መጣመርንና መዋሀድን በአጠቃላይ አንድነትን እና ኅብረትን እንደሚያመለክት የእምነቶ አባቶች ይገልጻሉ።


የደመራ በዓልም የደመራ እንጨቶች አንድ ላይ የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት መስቀል ቤተክርስቲያኗ ከምተከብራቸው የአደባባይ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ነው።


የመስቀል ደመራ በየዓመቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርአት ብዙ ህዝብ ተገኝቶ የሚያከብረው በዓል መሆኑንም አስታውሰዋል።


የዘንድሮው የደመራ በዓል ግን ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ አነስተኛ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ለኢዜአ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ እስከ 5 ሺህ ተሳታፊዎች በመስቀል አደባባይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት በዘንድሮ በዓል የተሳታፊ ሰዎች ቁጥር የተወሰነው ካለው ወቅታዊ የወረርሽኙ ሁኔታና መስቀል አደባባይ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ የሚችለውን መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን ይህንንም የጠቅላይ ቤተክህነት ለሚመለከተው አካል አሳውቋል።


የመስቀል አደባባይ ለበዓሉ ዕለት ክፍት እንደሚሆንና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መግለጹንና ይሄንንም በአካል ተገኝቶ መመልከቱን አስረድተዋል።


የመስቀል በዓል ሰላማዊና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አስረድተዋል።


በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከዚህ በፊት እንደነበረው ብዙ ህዝብ ተሰብስቦ ማክበር የማይቻል መሆኑን የእምነቱ ተከታዮች ተገንዝበው በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ አማራጮች የበዓሉን ስነ ስርዓት መከታታል እንደሚችሉ ነው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ያስገነዘቡት።


በበዓሉ የሚገኙ ምዕመናን ወደ መስቀል አደባባይ ሲመጡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎችን የራስ መከላከያዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር አካላዊ ጥግግትን በቀነሰ መልኩ ግብይት ለማድረግ አስቀድሞ ፒያሳ ይካሄድ የነበረውን የአትክልት ግብይት ሥፍራ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ወደ ጃንሜዳ ማዘዋወሩ የሚታወስ ነው።


ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል በየዓመቱ በድምቀት የሚከበርበትና ከአዲስ አበባ የተለያዩ አድባራትና ገዳማት የሚመጡ ታቦታት የሚያድሩበት ቦታ ነው።


ኢዜአ ዘንድሮ ከሚከበረው የጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ በዓሉ የሚከበርበትን ጃንሜዳ አስመልክቶ ለብፁዕ አቡነ አረጋዊ ጥያቄ አንስቷል።


በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ውይይት መደረጉንና ጊዜው ሳይደርስ ከወዲሁ እርምት መውሰድ እንደሚገባ ቤተክርስቲያኗ መግለጿን ተናግረዋል።

በዚህም የከተማ አስተዳሩ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱንና የግብይት ስፍራውን ወደ ሌላ አካባቢ የመቀየር ሥራ መጀመሩ እንደተገለጸላቸውም አመልክተዋል።

"የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሁን ትኩረቷ የመስቀል በዓል እንደሆነና ከበዓሉ መጠናቀቅ በኋላ ግን ሙሉ ለሙሉ ለጥምቀት በዓል ዝግጅት በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።


ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች የመስቀል በዓል የሰላም፣ የጤና፣ የበረከትና የረድኤት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም