ለዲቦራ ፋውንዴሽን ማጠናከሪያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ለዲቦራ ፋውንዴሽን ማጠናከሪያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሄደ
 
           አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2013(ኢዜአ) በአቶ አባዱላ ገመዳ ተመስርቶ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ለማገዝ ውጥን የያዘው ዲቦራ ፋውንዴሽን ማጠናከሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ላለፉት በርካታ ዓመታት በከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊነት ኢትዮጵያን ያገለገሉት አቶ አባዱላ ገመዳ አራተኛ ልጃቸው ከአእምሮ እድገት ውስንነት ጋር ተወለደች።
አቶ አባዱላ ልጃቸው ዲቦራን ከችግሩ ትላቀቅ ዘንድ በሕክምናው መንገድ ብዙ ሞክረው እንዳልተሳካና ችግሩ ዘላቂ መሆኑን ተረዱ።
ባለፈው ዓመትም መሰል በተፈጥሮ ከሚያጋጥም ችግር ጋር የሚወለዱ ሰዎችን ለማገዝ እንዲውል የዲቦራ ፋውንዴሽንን መስርተዋል።
በትናንትናው እለትም በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የፋውንዴሽኑ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ህጻናት ማሰልጠኛ ማዕከል አስመርቀዋል።
በተመሳሳይ በአቶ አባዱላ የተጻፈ 'ዲቦራ፤ የብርሃን ጉዞ' የተሰኘ በዲቦራና በአእምሮ እድገት ውስንነት ላይ ያተኮረ ሁለተኛ መጽሃፍ ተመርቋል።
ከመጽሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ፋውንዴሽኑን ለማጠናከርና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ለማገዝ እንደሚውል ተጠቁሟል።
አቶ አባዱላ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ፋውንዴሽኑ ከዚህ ችግር ጋር የተወለዱ ህጻናት ረጂ እንጂ ተረጂ እንዳይሆኑ የማስቻል ዓላማ አለው።
ትልቁ የፋውንዴሽኑ ራዕይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ለአገራቸው የሚጠቅሙ እንዲሆኑና ማህበረሰቡም እንደ ችግር እንዳይመለከተው ማድረግ መሆኑም አስረድተዋል።
ፋውንዴሽኑ ባለፈው አንድ አመትም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ህጻናት እየተንከባከበ ለሚገኘው 'ፍቅር በጎ አድራጎት ድርጅት' ሁለት ተሽከርካሪ ገዝቶ መስጠቱንም አስታውሰዋል።
በተመሳሳይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ህጻናት ቤተሰቦች የምግብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የፋውንዴሽኑ ዋና ማዕከል በለገጣፎ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል በተረከበው 60 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግንባታ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የድጋፍ ማሰባሰቢያው የፋውንዴሽኑን ዋና ማዕከል በአጭር ጊዜ ለመገንባት እንደሚውል ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፋውንዴሽኑን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ባለሃብቶችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ፋውንዴሽኑን ለማገዝ ቃል ገብተዋል።
እስካሁን ፋውንዴሽኑን ለደገፉ አካላት ምስጋና ተችሯቸዋል።