ቀጥታ፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራ ልዑክ በኛንጋቶም ወረዳ የልማት ሥራዎችን ጎበኘ

ሐዋሳ፣ መስከረም 10/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎበኘ።

የሥራ ኃላፊዎቹን ያካተተው ልዑክ በወረዳው ፕሱመሪያ ቀበሌ የኦሞ ወንዝን በመጠቀም በማኅበር ተደራጅተው የሙዝ ልማት እያካሄዱ ያሉ የሴቶች የሥራ እንቅስቃሴን ትናንት ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

ሙዝ አልሚ ሴት አርብቶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም በግብርና ልማት ተሳትፎ እንዳልነበራቸው ለልዑክ ቡድኑ ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ባደረገላቸው ድጋፍ በመታገዝ የግብርና ልማት ውስጥ መግባት እንደቻሉ አብራርተዋል።

በተሰማሩበት የሙዝ  ልማት ያጋጠማቸው የውኃ መሳቢያ ፓምፕ ችግር የበለጠ ውጤታማ እንዳይሆኑ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል ።

በመንደር እንዲሰባሰቡ ከተደረገም በኋላ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣ መጠለያና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች እንዳልተሟሉላቸው በመግለጽ ችግራቸው እንዲቃለልላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም አካባቢያቸው በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ተጉብኝቶ እንደማያውቅ የገለጹት ሴት አርብቶ አደሮቹ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና የሥራ ኃላፊዎቹ ወደ ሥፍራው በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው መንግሥት የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለመቀየር የመስኖ ልማት ሥራን ለመደገፍ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ሙዝ አምራቾች ያጋጠማቸውን  የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ችግር በቅርቡ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ በፀሀይ ኃይል የሚሰሩ ፓምፖችን ለማቅረብ ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በአካባቢው በስፋት እየለማ ላለው ለሙዝ ምርት የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በመንደር ማሰባሰብ መርሀ ግብር ለተቋቋሙ መንደሮችም የጋራ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶች ለማሟላት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በአካባቢው አንድ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋም ግንባታ ለማካሄድ በዕቅድ መያዙን ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም