ቀጥታ፡

በመተማ ከተማ 150 ሺህ ዶላር ወደ ሱዳን ሊያሸሽ የሞከረ ግለሰብ ተያዘ

መተማ፣ መስከረም 10/2013 (ኢዜአ)  በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር 150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማ አስተዳደተሩ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማንደፍሮ አንለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሕገወጥ ዶላሩ የተያዘው ትናንት ከቀኑ 6 ሰዓት አካባቢ ከመተማ ዮሐንስ ወደ ሱዳን ሊሻገር ሲል በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኬላ በተደረገ ፍተሻ ነው።

በፀጥታ መዋቅሩ ክትትል የተያዘው ተጠርጣሪ ግለሰብ ላይ በመተማ ዮሐንስ ፖሊስ ጣቢያ አስፈላጊው የሕግ ማጣራት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብር ኖቶችን መቀየር ተከትሎ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ሊደረግ የሚችልን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ከሌላው ጊዜ የተለየ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።

“ከባንክ ሲስተም ውጭ የሆነ በርካታ ብር ለሀገር ትርምስና ኮንትሮባንድ ንግድ ካልሆነ በስተቀር ለየትኛውም ሀገራዊ ዕድገት ፋይዳ የለውም” ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይም ማንኛውም ኅብረተሰብ ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ጥቆማ በመስጠት ሀገር የማዳን ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በርካታ የኢትዮጵያ ብር በጎረቤት ሀገራት መኖሩን ተከትሎ ከተማዋ ከሱዳን ጋር በቅርብ ርቀት የምትዋሰን የንግድ እንቅስቃሴ ያለባት በመሆኑ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የኢትዮጵያ ብር እንዳይገባና የውጭ ምንዛሪም እንዳይወጣ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ወደ ሱዳን በሕገወጥ መንገድ የተለያዩ ሸቀጦችና እንስሳት እንዲሁም የግብርና ምርቶች እንዳይሄዱም በኬላዎች የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጰያ አዲሱ የብር ኖት በዚህ ሣምንት ለግብይት መሠራጨት መጀመሩ የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም