የአፋር መንፈሳዊ መሪ ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አረፉ - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር መንፈሳዊ መሪ ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አረፉ
ሰመራ፣ መስከረም 10/2013(ኢዜአ) የአፋር መንፈሳዊ መሪ ባደረባቸው ህመም በአዲስ አበባ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ74 ዓመታቸው ትናንት ሌሊት ከዚህ አለም በሞት አረፉ።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ በሃገራችን የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ በስደት ከነበሩበት የውጭ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ከሁለት ዓመታት በፊት መሆኑ ይታወቃል።
በውጭ ሃገር ቆይታቸው ለአፋር ሕዝብ በጥቅል ለኢትዮጵያውያን መብት ሲታገሉ መቆየታችው የተገለጸው ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ወደ ሃገራቸው ከገቡ በኋላ ለውጡን ለማስቀጠል ከህዝባቸው ጋር ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ ከ2004 ጀምሮ ህዝባቸውን በመንፈሳዊ መሪነታቸው ያገለገሉ ሲሆን በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነውም ሰርተዋል።
የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነ-ስርዓት በትውልድ ስፍራቸው አይሳኢታ በነገው እለት እንደሚፈጸም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።