የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የደቡብ ክልል አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የደቡብ ክልል አመራሮች
ሐዋሳ፣ መስከረም 9/2013 (ኢዜአ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በደቡብ ክልል የሚገኙ አመራሮች ገለፁ።
በክልሉ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ ከድር የግደቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ የዞኑ ነዋሪዎች የቻሉትን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በቦንድ ግዥ፣ በገንዘብና በዓይነት ስጦታን ጨምሮ እስካሁን ከ92 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ መደረጉን ጠቅሰዋል።
"የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ አንድ ላይ ከሆን ሠርተን ማጠናቀቅ እንደምንችል ማሳያ ነው" ያሉት አቶ ዓሊ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።
ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ፋይዳው ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር ኢኮኖሚያዊ ጠቄሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግደቡ ግንባታ ቀሪ ስራ እንዲጠናቀቅ እየተደረገ ያለው ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የየም ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይሁን አሰፋ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የነበረው ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ መሀል ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ተከትሎ ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰዋል።
"ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግስት ክፍተቶችን ለማረም በወሰደው ቁርጠኛ አመራር የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሀ ሙሌት በመጠናቀቁ የህዝቡም ተሰፋ መልሶ ማንሰራራት ጀምሯል" ብዋል።
በዞኑ ህዝብ ዘንድ ዳግም ያንሰራራውን ተስፋ ተከትሎ ከዚህ ቀደም በቦንድ ግዥና በሌሎች አማራጮች ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ።
"የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በህብረተሰቡ ዘንድ ዳግም የፈጠረው መነሳሳት ለድጋፍ ስራው ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል" ያሉት ደግሞ የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚኪያስ እሥራኤል ናቸው።
በተያዘው 2013 ዓመት የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የሚካሄድበትና የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት የሚጀመርበት በመሆኑ የተለየ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ዕቅዶች በማውጣት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል።
ለመሰብሰብ የታቀደውን ገቢ ለማሳካት ህብረተሰቡንና በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታወቀዋል።
በደቡብ ክልል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ታውቋል ።