በሰሜን ሸዋ ዞን ከ17ሺ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ እየተደረገለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን ከ17ሺ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ እየተደረገለት ነው
ፍቼ፣ መስከረም ዐ9/2ዐ13 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከ17ሺ ሄክታር በላይ የተፈጥሮ ደን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ እንዳሉት በዞኑ የእርሻ መሬት ፍላጐት እያደገ መምጣት፣ ለግንባታና ማገዶ እንጨት ፍላጐት መጨመር እያስከተለ ያለውን የደን ውድመት ለመግታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ወሳኝ ነው።
ይህንን ለመተግበር በዞኑ 13 ወረዳዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት ከህብረተሰቡ የተውጣጣ የደን ጥበቃ ግብረ ኃይል በማቋቋም የተፈጥሮ ደን ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል፡፡
በተለይም የዞኑ ህዝብ ለዚህ ተግባር ከሁለት ሚሊዬን ብር በላይ በማዋጣት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም በአረንጓዴ የአሻራ ልማት መርሀ ግብር የተተከለ ችግኝ በማካተት የመንከባከብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱና በጐ አድራጊ ግለሰቦች የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ስለሚያስከትለው ጉዳት፣ የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅና መንከባከብ እንደሚቻል እንዲሁም ህብረተሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ ስለሚሆንበት ሁኔታ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአካባቢው ተዳፋት ቦታዎችን ከእርሻ ነፃ በማድረግ ባለፈው ዓመት ከሰማንያ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዛፍ ችግኝ ተሸፍኖ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ ሆኖ እየተጠበቀ መሆኑን አቶ ሄርጳሳ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ክረምት ከተተከለው 11ዐ ሚሊዬን ሀገር በቀልና የውጪ ዝርያ ያለው የዛፍ ችግኝ ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ ማጽደቅ መቻሉን አመልክተዋል።
ማጽደቅ የተቻለው ህብረተሰቡ አካባቢውን ከእንስሳት ንክኪ በመከለል ችግኙን ውሃ በማጠጣት፣ በማረምና በመኮትኮት ባደረገው እንክብካቤ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከጸደቀው ችግኝ መካከል ዋንዛ፣ ግራር፣ ወይራና ባህር ዛፍ ይገኝባታል፡፡
በዞኑ እስከ 2ዐ15 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ66 ሺህ ሄክታር በላይ የደን ችግኝ በማልማት ጥበቃና እንክብካቤ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማድረግ ታቅዷል፡፡
በደን ጥበቃ ሥራ ከተሰማሩት ነዋሪዎች መካከል በወረጃርሶ ወረዳ የኖኖ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ ቶልቻ በሰጡት አስተያየት ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክር ደንና ችግኝ በመንከባከብ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደኑ መኖር ምርታቸው እንዲጨምር ፣ የአካባቢ አየር እንዲስተካከልና ዝናብ እንዲኖር እንደሚያደርግ ግንዛቤ በመጨበጣቸው ደኑን በራሳቸው ተነሳሽነት በሣምንት ሁለት ቀን እንደሚጠብቁም ጠቅሰዋል፡፡
ዲያቆን ተሰማ ዱፌራ በበኩሉ የክረምት የእረፍት ጊዜውን በእምነት ቦታዎች በሚካሄድ የችግኝ ተከላ ስነ-ስርዓት በመሳተፍ ማሳለፉን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም የተተከለውን ችግኝ ህብረተሰቡ እንዲንከባከብ በሚያገኘው መድረክ ሁሉ እንደሚያስተምር ገልጿል፡፡