የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2020 ትርፋማ ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2020 ትርፋማ ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ ሆነ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓዊያኑ 2020 የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተቋቁመው ትርፋማ ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ መሆኑን ፎርብስ አስታወቀ፡፡
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ድንበሮች በመዘጋታቸውና የጉዞ ክልከላ በመደረጉ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተዳክሟል፣ በዚህም ግዙፍ የሚባሉ አየር መንገዶች ሳይቀሩ ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡
ነገር ግን ወረርሽኙን ተቋቁመው ትርፋማ ከሆኑ አየር መንገዶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ መሆኑን ፎርብስ መፅሄት አስነብቧል፡፡
አየር መንገዱ ትርፋማ የሆነው የአገልግሎት ስብጥሩን በማስፋቱ መሆኑንም መጽሄቱ አብራርቷል።
አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ ቋሚ ወጭዎቹን ሸፍኖ መጠነኛ ትርፍ ማስመዝገቡም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም "ያሰብነውን ያህል ትርፍ አላስመዘገብንም፣ ነገር ግን መጠነኛ ትርፍ አግኝተናል በተለይ የጭነት አገልግሎታችን በጥሩ ሁኔታ ሰርቷል" ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየሳምንቱ 40 የሚጠጉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በረራዎችን ሲያደርግ ተቀናቃኞቹ ግን አውሮፕላኖቻቸውን ከበረራ ውጭ ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
አየር መንገዱ በዓመቱ ከበረራ ትኬት ሽያጭ ያገኝ የነበረውን 1 ቢሊዮን ዶላር ማጣቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ነገር ግን ተመሳሳይ አለም አቀፍ አየር መንገዶች 84 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኪሳራ እንደደረሰባቸው አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር ማስታወቁም ተገልጿል፡፡