ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት ፅዳት አከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት ፅዳት አከናውነዋል
አዲስ አበባ መስከረም 9/2013 (ኢዜአ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የዓለም የጽዳት ቀንን" በማስመልከት በልደታ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ፅዳት አካሄዱ።
ምክትል ከንቲባዋ በፅዳት ሥራዎች ትብብር ላደረጉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን (ኢዜአ) ጨምሮ ለአምስት የመገናኛ ብዙኃን የእውቅና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፉ የፅዳት ቀን በዛሬው እለት በዓለም ዙሪያ 190 አገሮች ተሳትፈውበት ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ በዓለም ላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈው "ፕላኔታችንን እናፅዳ" በሚል መርህ በተለያዩ አገራት ተከናውኗል።
ይህንን ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር መሰረት በማድርግም የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ፅዳት አከናውነዋል።
በዚህ አጋጣሚ አገራችንን ብሎም ከተማችንን በዘላቂነት ለማፅዳት የምንተጋበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዓመቱ መጀመሪያ ቃል ከተገባው አንዱና ዋነኛው አካባቢን ከቆሻሻ በማጽዳት ውብና ፅዱ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም አዲስ አበባን የፀዳች ከተማ ለማድረግ የአንድ ቀን ክንውን ብቻ በቂ ባለመሆኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በኮሮናቫይረስ መከሰት ምክንያት ትምህርት ቤቶች ታማሚዎችን ለማቆያነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከዓለም ተሞክሮ ተወስዶ ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋለ።
ለዚህም የትምህርት ቤቶቻችንን ጽዳት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማዋ አካባቢያቸውንና መንደራቸውን በማፅዳት ወደ አረንጓዴነት የቀየሩ ለአሥር ወረዳዎችና ለስምንት ድርጅቶች የዋንጫና የሰርቲ ፊኬትሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባትን ወክሎ ሽልማቱን የተቀበለው ወጣት ኢፋ አቢሼ ሽልማቱ ወደ ፊት አካባቢን ከቆሻሻ ለማጽዳት ለሚደረገው ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብና ማስወገድ ድርጅት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አስቻለው ባዩም ሽልማቱ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት ላከናወናቸው የፅዳት ሥራዎች ትብብር ያደረጉ ኢዜአን ጨመሮ አምስት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የእውቅና የምስክር ወረቀት በምክትል ከንቲባዋ ተበርከቶላቸዋል።