ቀጥታ፡

ህፃናትን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ ለሚከናወን ስራ 129 ሚሊዮን ብር ተመደበ

መቀሌ፣ መስከረም 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም መሰረት በትግራይ ክልል እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ከመቀንጨር ችግር ለመታደግ ለሚከናወን ስራ ማስፈጸሚያ 129 ሚሊዮን ብር መመደቡ ተገለጸ።

የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ፀጋዝአብ ኃይሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ የሚከናወነው በክልሉ ከፍተኛ የህጻናት የመቀጨር ችግር ባለባቸው ወረዳዎች ውስጥ ነው።

ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ ከተመደበው በጀት ውስጥ  28 በመቶ ያህሉ በፌደራል መንግስት ቀሪው በክልሉ የሚሸፈን ነው ብለዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት  ብቻ በፕሮግራሙ ችግረኛ እናቶችና ህጻናትን  ጨምሮ በጠቅላላ 357 ሺህ ተጠቃሚዎች እንደሚታቀፉ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ280 ሺህ በላይ  እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ናቸው።

በክልሉ በ2010 ዓ.ም በስድስት ወረዳዎች የተጀመረው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ዘንድሮ በ21 ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ  ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮግራሙ በ2012 በጀት ዓመት  132 ሚሊዮን 500 ሺህ  ብር ወጪ በስምንት ወረዳዎች  ውስጥ የመቀንጨር መጠን ለመቀነስ እናቶችን በማሳተፍ የግብርና፣ ጤና፣ትምህርት ፣መጠጥ ውሃና ሌሎችም  የልማት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ልጆቻቸውን ከመቀንጨር ለመታደግ  በተመሳሳይ የስራ ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን እንደሚከናወኑ አስተባባሪው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብና ጤና አገልግሎት ተቋም በ2011 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት የትግራይ ክልል የህፃናት የመቀንጨር መጠን 49 በመቶ ነው ያሉት አስተባባሪው፤ የችግሩ መጠን በጣም ከፍተኛ በመሆኑ መቀንጨርን በ2022 ዓ.ም ከክልሉ ለማጥፋት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት  የሁሉም ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

መቀንጨርን ለማጥፋት ፕሮግራሙ በእንስሳት እርባታና አትክልት ማምረት ስራ ትኩረት አድርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ አታክልቲ ገብረልኡል ናቸው።

አቶ አታክልቲ እንዳሉት መቀንጨርን ለመቀነስ ከዶሮ ፣ ፍየል፣ በግ፣ ከብት እና ንብ እርባታ በተጨማሪ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተሰማርተው አትክልትና ፍራሬዎች አምርተው ልጆቻቸውን በአግባቡ እንዲመግቡ  እየተደረገ ነው።

በምዕራባዊ ዞን የላዕላይ ፀለምት ወረዳ ነዋሪ አቶ ምህረት ዘለቀ  በሰጡት አስተያየት " ሁለት ዓመት ያልሞላቸው መንትያ ህፃናት ስላሉኝ በፕሮግራሙ ታቅፌ ልጆቼ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው"  ብለዋል።

ከተሰጣቸው 25 የእርባታ ዶሮዎች የሚያገኙትን  እንቁላል  ልጆቻቸው በመመገብ የተረፋቸውን ደግሞ በመሸጥ ሌሎች ለህፃናቱ  የሚጠቅሙ የምግብ ዓይነቶች  በመግዛት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ  እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

በፕራግራሙ ድጋፍ ልጆቻችን በቅርበት ለመማር የሚያስችላቸውን የመማሪያ ክፍሎች በአካባቢያቸው መገንባታቸውን የገለጹት ደግሞ  በጣንቋ በርገሌ ወረዳ ስምረት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገብረ ሚካኤል ንጉስ ናቸው።

ሰቆጣ ቃል ኪዳን በ2030 ዓ.ም የመቀንጨር በሽታን ከኢትዮጰያ ለማጥፋት ግብ ይዞ በ2010 ዓ.ም በተከዜ ተፋሰስ የሚገኙ የትግራይና አማራ ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ መንቀሳቀስ የጀመረ ፕሮግራም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም