"አዲስ አበባን እንደስሟ ጽዱ እናድርጋት"... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

66

መስከረም 9/ 2013 (ኢዜአ) "አዲስ አበባን እንደስሟ ጽዱ እናድርጋት" ሲሉም የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዓለም አቀፉን የጽዳት ቀን በማስመልከት ዛሬ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የጽዳት ዘመቻው ተሂዷል።

የጽዳት ዘመቻውን የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ ዓለሙ በልደታ ክ/ከተማ ተገኝተው አስጀምረዋል።

በባልቻ አባነፍሶ ሁለተኛ እና መሠናዶ ት/ቤት በተከናወነው የጽዳት ዘመቻው ላይ የከተማ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ከአዲስ አበባ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን እንደስሟ ጽዱ እናድርጋት ሲሉም ተናግረዋል።

በዛሬው እለት የከተማዋ ነዋሪዎች የአለም ማህበረሰብ ተቀላቅለን አካባቢያችንን እና ከተማችንን አጽድተናል ያሉት ምክትል ከንቲባዋ "በቅርብ የምንከፍታቸውን ትምህርት ቤቶች የማጽዳት እና የጸረ ተሕዋሲያን ኬሚካል ርጭት ስራ አካሂደናል "ብለዋል።

ባሳለፍነው ዓመት ታትረው የጽዳት ስራ ሲሰሩ የነበሩ ነዋሪዎችን አመስግነው፤ ከዛሬ ጀምሮ ሁላችንም በመተባበር እና በአንድነት መንፈስ አዲስ አበባ ስሟን እና ክብሯን የሚመጥን ጽዳት እንዲኖራት እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በከተማ ደረጃ 108 የጽዳት ሞዴል የሆኑ መንደሮች የተለዩ መሆናቸውና ከእነዚህ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ሥራቸውን ላከናወኑ ስምንት ሞዴሎች እውቅና እንደሚሰጥ ትናንት መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም