ቀጥታ፡

አባገዳዎችና አርቲስቶች በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች ማሳያ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013(ኢዜአ) በግንባታ ላይ ያሉት የባህል እሴቶች ማሰልጠኛና ማምረቻ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የኦሮሞን ህዝብ ውበት ከመግለጽ ባለፈ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን አባገዳዎች ተናገሩ።

በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ባለቤትነት በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የኦሮሞ ባህላዊ ምግብና አልባሳት ማሰልጠኛና ማምረቻ ማእከላት እንዲሁም የአርት ትምህርት ቤት የግንባታ ፕሮጀክቶች ዛሬ በአባ ገዳዎችና አርቲስቶች ተጎብኝተዋል።

በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል በቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚገነባው የኦሮሞ ባህላዊ ምግብ ማዘጋጃ፣ ማሰልጠኛና መሸጫ ማዕከል፣ በመስቀል ፍላወር እየተገነባ ያለው የኦሮሞ አርት ትምህርት ቤት እንዲሁም ልደታ አካባቢ እየተገነባ ያለው የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ማምረቻ፣ ማሳያና ማሰልጠኛ ህንጻ ግንባታዎች ይገኛሉ።

በጉብኝቱ የተሳተፉትም ከስምንቱ የኦሮሞ ገዳ አርዳ ጂላዎች ኃላፊ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ አርቲስቶች እንዲሁም ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተወከሉ ናቸው።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ጸሐፊ አባ ገዳ ጎበና ሆላ እንዳሉት በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ የኦሮሞን ህዝብ እሴትና ውበት ከመግለጽ ባለፈ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ተጠናቀው ወደስራ እንዲገቡ የህዝቡ ድጋፍ አይለየውም ብለዋል። 

ከሲኮ መንዶ ገዳ የኦዳ ሮባ አባ ገዳ አሊይ መሐመድ ሱሩር በበኩላቸው የባህል እሴት ፕሮጀክቶቹ የኦሮሞ ህዝብ የረጅም ዓመት ጥያቄን የመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“በፕሮጀክቶቹ ግንባታ የተሰማን ደስታ ወደር የለውም ያሉት” ደግሞ ከሀረርጌ የመጡት የአርፈን ቀሎ አባ ገዳ አብዱራዛቅ አህመድ ሐሰን ሲሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችን አይለየውም ብለዋል።

ከኦሮሞ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማህበር የተወከለው አርቲስት ቀሮ ታመነ በበኩሉ በተለይም የአርት ትምህርት ቤቱ የመለማመጃ መማሪያና መተወኛ የብዙ ጊዜ ጥያቄያችንን የመለሰና እጦታችንን ያረካ ነው ብሏል።

ፕሮጀክቶቹን በበላይነት እያስገነባ ያለው የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ቡጤ እንዳሉት አብሮነትን በተግባር ሲኖረው የነበረና የጎላ ባህላዊ እሴት ያለው የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች ማሳያ ግንባታ ለሌሎቹም ብሔሮች ልምድና ተሞክሮ መቀመሪያ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ የእሬቻን እሴቶች ምልዓት የሚያሳዩ የባህላዊ ምግብና አልባሳት ማዘጋጃ፣ ማሰልጠኛና መሸጫ እንዲሁም የኦሮሞ አርት ትምህርት ቤት የሚያሳዩ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም