ቀጥታ፡

ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ የሚያመጡ ተቋማትና ግለሰቦች ህጋዊ የሽያጭ ሰነድ ማረጋገጫ ካቀረቡ ህጋዊ ናቸው---ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) መንግስት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በቤት መቀመጥ የለበትም በማለት ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ከተጠቀሰው ብር በላይ ወደ ባንክ የሚያመጡ ተቋማትና ግለሰቦች ህጋዊ የእለት ሽያጭ ማረጋገጫ ካቀረቡ ህጋዊ መሆናቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ከ100 ሺህ አስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ በእጁ ያለው ግለሰብም ሆነ ድርጅት ህጋዊ መሆኑም ተመልክቷል።

አዲሱን የብር ኖቶች ቅያሬ ለውጥ ተከትሎ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ከዕለት ሽያጭ መገኘቱን የሚያሳይ ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ተቋማትና ግለሰቦች ገንዘቡን ወደ ባንክ ማስገባት ይችላሉ ተብሏል፡፡

ከተጠቀሰው ብር በላይ ሲያመጡ ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ የማይችሉ ተቋማትና ግለሰቦች ያመጡት ገንዘብ ህገወጥ በመሆኑ እንደሚወረስባቸውም ተገልጿል፡፡

አዳዲሶቹን የገንዘብ ኖቶች ስርጭት አየተሰራ ያለውን  ሥራ  በተመለከተ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ያለው ገንዘብ ህጋዊ ገጽታ ያለውና ህጋዊ ገጽታ የሌለው ተብሎ ተለይቷል፡፡

በዚህም ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በታች የሚያመጣ ማንኛውም አካል ገንዘቡን በባንክ አካውንቱ ማስቀመጥ የሚችል ሲሆን ከተጠቀሰው በላይ ገንዘብ ይዞ የሚመጣ ማንኛውም አካል የገንዘቡን ህጋዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡

ይህን ማድረግ የማይችል አካል ገንዘቡ ህገወጥ በመሆኑ እንደሚወረስ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ከ100 ሺህ አስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ በእጁ ያለው ግለሰብም ሆነ ድርጅት ህጋዊ መሆኑም የተናገሩት የባንክ ገዥው፣ ገንዘቡን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ወደባንክ በማምጣት መቀየር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተለያዩ ባንኮች በርካታ የባንክ ደብተር ያላቸው ግለሰቦች በቂ መረጃ ማቅረብ ካልቻሉ ገንዘባቸውን ከአንድ ባንክ ውጭ ማስገባት እንደማይችሉም ተገልጿል፡፡

ከወጣው መመሪያ አንፃር ከፍተቶች መታየታቸው በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን በተለይ አንዳንድ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በገደብ ከተቀመጠው ብር በላይ የመቀበል አዝማሚያ እያሳዩ በመሆኑ መመሪያውን እንዲያከብሩ ዶክተር ይናገር አሳስበዋል፡፡

ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተገልጿል፡፡

ከጎረቤት አገራት በተለይ በጅቡቲ፣ ሶማሌላንድና በቶጎውጫሌ በርካታ የኢትዮጵያ ብር የሚዘዋወር በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡

ይህን ተከትሎ ወደ ጅቡቲ የሚሄዱ አሽከርካሪዎች 30 ሺህ ብር ይዘው መውጣት የተፈቀደላቸው ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን ከ10 ሺህ ብር በላይ ይዘው መግባት እንደማይችሉ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ይህን ለማድረግ የሚሞክሩና ሲያደርጉ በተገኙ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል፡፡

ዶክተር ይናገር አዲሶቹ የብር ኖቶች በቀለም፣ በምስልና በደህንነት የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተላብሰው እንዲታተሙ መደረጉንና የተለዩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ፡

በሁሉም ባንኮች የሚከናወነውን የገንዘብ ዝውውር የሚከታተል ግብረ ኃይል ከብሔራዊ ባንክ ተቋቁሞ ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

ግብረ ኃይሉ ስራውን በየሁለት ቀኑ ተገናኝቶ እንደሚገመግም በመግለጫው ተጠቅሷል ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው "የገንዘብ ቅያሬው ጤናማ የባንክና የፋይናስ ሥርአት እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ ህገወጥ ገንዘብ እንዲመክን ያድርጋል" ብለዋል።

"የገንዘብ ቅየራ ስራው በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ በዚህም በዋናነት የሚጠቀሙት ህብረተሰቡና ህጋዊ የኢኮኖሚ ተዋንያን በመሆናቸው የገንዘብ ለውጡን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የብር ኖቶችን የመቀየር ሥራው የህግ የበላይነት የሰፈነበት የኢኮኖሚ ሥርአት ለመፍጠር እንደሚጠቅም ገልጸው፣ በቀጣይ የክፍያ ሥርአቱን የማዘመን ሥራም ጎን ለጎን እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም