ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰዓታት በኋላ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይጎበኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰዓታት በኋላ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይጎበኛሉ
አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2010 ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ የገቡት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰዓታት በኋላ ወደሀዋሳ ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የሀገሪቱ መንግስት ልዑክ በሀዋሳ ቆይታው በርካታ ዓለም ዓቀፍ አምራች ኩባንያዎች የሚገኙበትን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ይጎበኛል። የሀዋሳ ኢንዱስተሪ ፓርክ ከ18 በላይ ሼዶችን ያያዘ ሲሆን ምርቶቻቸውንም ወደ ተለያዩ አጋራት የሚልኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉበት ነው። ኢትዮጵያ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቁን ድርሻ የሚኖራቸው በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በየልማት ኮሪደሮቹ በመገንባት ላይ ናት። በዘርፉ ለመበልጸግ ላለመችው ግብ ፓርኩ ትልቁ ማሳያ ነው። ከነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀዳሚውና ከአገርም አልፎ በቀጠናው ሰፊ ልምድ እየተቀሰመበት የሚገኘው የሀዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ፓርኩንም የተለያዩ አገራት መሪዎችና በአገር ውስጥ ያሉ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለኃብቶችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ያሉ ሰራተኞች እየጎበኙት ልምድ እየወሰዱ ቆይተዋል። ከነዚህ ውስጥም የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤሌን ጆንሰን ሰርሊፍ እና የኤርትራ ልዑካን ቡድን አባላት በቅርቡ ፓርኩን ከጎበኙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ሲገቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የክልል ፕሬዝዳንቶችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የከተማው ህዝብ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሀዋሳም ተመሳሳይ አቀባበል አንደሚደረግላቸው የከተማው ነዋሪዎች ገልፀዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት ነው።