የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት የመስቀል ደመራ በአልን ማክበር በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት የመስቀል ደመራ በአልን ማክበር በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
በዚህም የፊታችን መስከረም 16 ቀን የሚከበረው የመስቀል ደመራ በአል የማክበሪያ ስፍራ ዝግጅትን ጎብኝተዋል፡፡
አሁን ላይ ስፍራው የመስቀል ደመራ በአልን ማክበር በሚያስችል መልኩ ተዘጋጀቶ ማየታቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጽእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስፍራው ለደመራ በአል ዝግጁ መሆን ገልጸው፤ በአሉም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በአነስተኛ ቁጥር ሰዎች እንደሚከበርም ጠቅሰዋል፡፡
ግንባታው ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን የተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋን ገጽታ በመገንባትና ተጨማሪ ገጽታ በመፍጠርም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተጀመረ 3 ወራትን ቢያስቆጥርም የከተማ አስተዳደሩ በገባው ቃል መሠረት ግንባታውን በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የግንባታው ፍጥነትም ለበአል ቶሎ ለማድረስ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ እንደሚሻገር ፕሮጀክት በጥንቃቄ እየተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የቤተክርስቲያኒቷ የሃይማኖት አባቶች መሳተፋቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።