ምክር ቤቱ አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎችን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር በቀረበ ምክረ ሀሳብ ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አምስተኛ አመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ አስቸኳይ ስብሰባው ከጤና ሚኒስቴር በቀረበለት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ዶክተር ሊያ አጠቃላይና ዝርዝር ምክረ ሀሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን ትምህርት ቤቶችን ስለመክፈትና አገራዊ ምርጫን ማካሄድን በተመለከተም በዝርዝር አቅርበዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
ትምህርት ለመጀመር ከመወሰኑ በፊት ግን ጠንካራ ግብረ ኃይል በየደረጃው ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባት እንዳለበት ነው ሚኒስትሯ ያስታወቁት።
አገራዊ ምርጫ ማካሄድን በተመለከተም ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች በተለየ መልኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል ከግምት ያስገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ቋሚ ኮሚቴ እና ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርቡ መርቷል።