ቢሮው ትምህርት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

78

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) የ2013 የትምህርት ዘመን ትምህርት ለማስጀመር የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የተደረሰው ትምህርት የማስጀመር ውሳኔ ተከትሎ ከተማ መስተዳድሩ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ ገልፀዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረው የወላጅ ጭንቀት እንደሚጋሩ የገለፁት የቢሮ ሃላፊው አጠቃላይ የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ትምህርት ለማስጀመር አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር በወረደው አቅጣጫ መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪዎች ብቻ እንደሚማሩ አንስተው ሂደቱም በሁለት ፈረቃ ምናልባትም በሶስት ፈረቃ በጥንቃቄ መንገድ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡

በመንግስት ትምህርት ቤቶች በኩል የትምህርት መጀመር ታሳቢ በማድረግ በለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች የማስለቀቅና በኬሚካል በማፅዳት ምድረጊቢውን ንፁህ አድርጎ ለተማሪዎች ዝግጁ የማድረግ ስራዎች ለማከናወን በከተማ ደረጃ የንቅናቄ እቅድ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡

በአንዳንድ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በኩልም ከምዝገባ ሂደት ጎንለጎን በከተማዋ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የመማርያ ክፍል እጥረት ያጋጥማቸዋል ተብሎ የታሰቡትን የግንባታ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ንቅናቄ በመፍጠር ህብረተሰቡ ያለስጋት ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ ማድረግና በትምህርት ቤቶች በኩል የተለያዩ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ይሰራል ብለዋል፡፡

የመማር ማስተማር ሂደቱ በፈረቃ ሲደረግ የሰው ሃይል እጥረት እንዳያጋጥም በአገር ደረጃ የመጣ የዜግነት ግዴታ በመሆኑ አስተማሪዎች በሁለቱም ፈረቃ ሊሰሩ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

የበሽታው ስርጭት ለመግታት ሊፈጠር የሚችለው የውሃ መቆራረጥ ለማስቀረት ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀት በ148 ትምህርት ቤቶች ላይ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ ውሃ ለማግኘት መታሰቡንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የውሃ አቅርቦቱ ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ትምህርት ቤት 5 ሺህ ሊትር የሚይዝ ሮቶ ግራና ቀኝ በማድረግ ተማሪዎች ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ንፅህናቸው እንዲጠብቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡

“ስላሽ ኢትዮጵያ” ከተባለ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ከተማሪዎች ቁጥር አንፃር በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ምን ያህል የመጸዳጃ ቤት ብዛት፣ የመታጠብያ ውሃ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የወረርሽኙ ማብቂያ ስለማይታወቅ ወላጆች ልጆቻቸው ትምህርት ባይጀምሩም በቤትም ሆነ ከቤት ውጭ በሚኖራቸው እንቅስቃሴ ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረጉ በቫይረሱ መያዛቸው አይቀሬ በመሆኑ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ኮቪድ ውስጥ ሆነን የምናገኛቸው ማህበራዊ አገልግሎት አማራጭ እንደሌለው አንስተው የሙቀት መለኪያ፣ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘርና የፊት ጭምብል ለመንግስትም ሆነ ለግል ትምህርትቤቶች በነፃ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም