ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ህፃናትን ለመታደግ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ትብብር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ህፃናትን ለመታደግ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ትብብር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2012(ኢዜአ) በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ህፃናትን ለመታደግ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ትብብር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
ከቀያቸው ለተፈናቀሉና በስደተኛ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ ማሰባሰቢያና የማንቂያ ዝግጅት በዌብናር ተካሂዷል።
"Education cannot wait" በተሰኘ ድርጅት አማካኝነት በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ)፣ የቦርኪናፋሶና የሶማሊያ ትምህርት ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ ወጣቶችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ግለሰቦች ተሳትፈዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ ትምህርት ልዩ መልዕክተኛና የድርጅቱ ሊቀመንበር ጎርደን ብራወን 4 ሚሊዮን 5 00 ሽህ ህፃናት በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው በመፈናቀላቸው አስቸኳይ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለህፃናት የምትመች አለምን ለመፍጠርም መስራት ይገባልም ነው ያሉት።
በዌብናሩ የቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ) ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን የምታስናግድ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው በስደተኛ ካምፕ ውስጥና በተለያዩ ችግር ውስጥ ያሉ ህፃናት ትምህርት እንዲያገኙ አጋር አካላት የሚያደርጉትት ድጋፍ አመስግነዋል።
የኮቪድ -19 ተፅዕኖ የተጨመረበትን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትብብርና የፖለቲካ ቁርጥኝነት እንደሚያስፈልግ የዝግጅቱ ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
በገንዘብ ማሰባሰቢያና የማንቂያ ዝግጅቱ ላይ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድና ኖሮዌይ የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋለል።
ችግር መፍትሄን ይዞ ይመጣል ያሉት የEducation cannot wait`` ዳይሬክተር ያስሚን ሸሪፍ የህፃናትን የወደፊት እጣ ፈንታን አሁን ማስተካከል አለብን ብለዋል።