በ550 ሚሊዮን ዶላር በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመስኖና የእንስሳት ሀብት ልማት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው

67
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 በ550 ሚሊዮን ዶላር በጀት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ሰፋፊ የመስኖ ስራዎችና የእንስሳት ሀብት ልማት ለማከናወን የሚያስችል ፕሮጀክት እየተዘጋጀ መሆኑን የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለፀ። ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት የተከናወኑ ስራዎችን መሰረት ያደረገ ጥናት ተካሂዶ በቀጣይ ምን መስራት እንደሚያስፈልግ በመለየት  ነው እየተዘጋጀ ያለው። ከአለም ባንክና ከአለም እርሻ ልማት ፈንድ በተገኘ የ550 ሚሊዮን ዶላር ብድር በስድስት አመታት ጊዜ ውስጥ የሚከናወን እንደሆነ ጠቁመዋል። ወደተግባር ለመግባት ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተውጣጡ አባላትን የያዘ ቡድን የፕሮጀክት አፈፃፀም መርሃ ግብር እያዘጋጀ ስለመሆኑ አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ አርብቶ አደሩን በዘላቂነት ከድርቅ ስጋት ለማላቀቅ ከዚህ በፊት በአነስተኛ መጠን ሲሰሩ የነበሩ የመስኖ ስራዎች፣ የእንሰሳት ሀብት ልማት ስራዎችን ላቅ ባለ ደረጃ በማስፋት አርብቶ አደሩን የገበያ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል። የሚሰራው ስራ አርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ደረጃ እንደሆነም አስረድተዋል። ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ከባለድርሻ አካላትና ከተጠቃሚዎች ጋር ውይይት መጀመሩን ጠቁመው በ2012 ዓ.ም ወደ ስራ እንደሚገባ ገልፀዋል። በፕሮጀክቱ አርብቶ አደሩን ብቻ ሳይሆን ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎችንም ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ካይዳኪ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም