ቀጥታ፡

በመተከል ዞን ጥቃት አድራሽ ሀይሉ በቂ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ፣ በእቅድ፣ በበቂ ሎጂስቲክስና በጀት የሚመራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከሚገኙ ፀረ ለውጥ ኃይሎች ጋር ትስስር ያለው ነው ተባለ

መስከረም 7/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ኤጳራ ቀበሌ ውስጥ ሞጂ እና ኮሼቦንጂ በተባሉ መንደሮች የሚኖሩ ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት አድራሹ ኃይል በቂ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ፣ በእቅድ፣ በበቂ ሎጂስቲክስና በጀት የሚመራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከሚገኙ ፀረ ለውጥ ኃይሎች ጋር ትስስር ያለው መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናገሩ።

ይህ ኃይል በክልሉ ውስጥ የሚገኙና የተገኙበትን ማኅበረሰብ የማይወክሉ ለሆዳቸው ያደሩ ቅጥረኞችን በመጠቀም የሚሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጠረውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እና በክልሉ ሰሞኑን የተከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ በማስመልከት ዋና ዳይሬክተሩ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በክልሉ መተከል ዞን በንጹሀን ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተሰማቸውን መሪር ሀዘን የገለጹት አቶ ግዛቸው ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በተጠቀሱት መንደሮች የሚኖሩ ንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው የተናገሩት አቶ ግዛቸው ጥቃት አድራሹ ኃይል በቂ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደ፣ በእቅድ፣ በበቂ ሎጂስቲክስና በጀት የሚመራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከሚገኙ የፀረ ለውጥ ኃይሎች ጋር ትስስር ያለው ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ኃይል አሰማርተው ሀገር ለማተራመስና የህዝቡን ማኅበራዊ ሰላም ለመንሳት የሚሠሩ ኃይሎች ትናንትም ሲያደርጉት የነበረ፤ ዛሬም እያደረጉት ያለ ሀገር ለማፍረስ የሚደረግ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ኃይሎች የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ናቸውም ያሉ ሲሆን ይህ ተግባራቸው ሀገሪቱን የማፍረስ ራእያቸውን ለማሳካት የሚሄዱበት ጉዞ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወደፊትም መልክ እየቀያየሩ በህዝቦች መካከል እንዲህ አይነት ግድያዎችን እየፈጸሙ ለመቀጠል ፍላጎት ያላቸው ስለሆነ እነዚህን ኃይሎች እንደትናንቱ እና እንደዛሬው እንዳይቀጥሉ ለማድረግ የመንግሥትና የህዝቡ ርብርብ ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተፈጸመው አሳዛኝና ድርጊት በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን እንደሞቱ በተለያዩ ሚዲያዎች እየተገለፀ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፤ የሟቾችን ቁጥርም ሆነ የደረሰውን አጠቃላይ የንብረት ውድመት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለህዝብ ለማሳወቅ መረጃ ተሰባስቦ ሲጠናቀቅ ለህዝብ የሚገለጽ ይሆናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም