ቀጥታ፡

ከቤንሻንጉል ጉምዝ በፀጥታ ችግር ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መኖሪያቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ መስከረም  7/2013 (ኢዜአ) ከቤንሻንጉል ጉምዝ በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መኖሪያቸው መመለሱን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ::

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈጠሩ ችግሮችን ለማረጋጋት የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ ሰሞነኛ ጉዳዮችን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች አቅም በላይ አልነበረም ሊከሰትም አይገባው ነበር ብለዋል።

ችግሩ በተፈጠረበት ሰዓት መከላከያ የራሱ ተልዕኮ ላይ ነበር ያሉት ሜጀር ጀኔራሉ ሠራዊቱ ወደ ስፍራው በማቅናት የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ስራ በጀግንነት ተሰርቷል ብለዋል።

መከላከያ ከገባ በኋላ በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰዱ አሁን በክልሉ ያለው ሁኔታ ወደ ቀድሞ ሰላማዊና መረጋጋት እንቅስቃሴ መመለሱንም አስታውቀዋል። በማህበራዊ ሚዲያዎች “መካላከያ ቀድሞ ወደ ስፍራው አልደረሰም” በሚል እየተናፈሰ ያለው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑንም ነው ሜጀር ጄነራሉ የተናገሩት።

በክልሎች የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ የማረጋጋት ግዴታ በዋናነት የክልልና የወረዳ የጸጥታ ኃይል ነው ያሉት ሜጀር ጄነራሉ መከላከያ የራሱ ግዳጆች ቢኖሩትም ከክልሎቹ አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ ችግር ሲያጋጥም አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መከላከያ ግዳጅ እንደተሰጠው ከ150 ኪሎ ሜትር ውስጥ 50 ኪሎ ሜትሩን በእግሩ በመጓዝ በታጣቂዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱንም ነው የተገለፀው።በአሁኑ ሰአት አካባቢው ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለሱን ነው ሜጀር ጀኔራል መሀመድ ተሰማ በመግለጫቸው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም