በኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት ላይ ግልጽነት መፈጠር እንዳለበት ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት ላይ ግልጽነት መፈጠር እንዳለበት ተጠቆመ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) በኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት ላይ ሙሉ ለሙሉ ግልጽነት መፍጠር ይገባል ሲሉ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማህበራት ተናገሩ።
አራት አገር አቀፍና እና ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማህበራት የኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደትን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ማህበራቱ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዝ አሶሴሽን፣ ዓለም ዓቀፉ የኤድስ ጤና ክብካቤ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ፣ የስነ-ተዋልዶ ጤና ማህበር እና ፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ ናቸው።
መንግስታትና የግል ድርጅቶች ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶችን ወደ ጎን በመተው የኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት ውጤት እንዲያመጣ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ የሲቪክ ማህበራቱ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሄልዝ አሶሴሽን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን በአዳዲስ የክትባት ምርት ሂደት ላይ በትብብር መሰራት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡
በተለይ "በኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት ላይ ተገቢ የሆነ ግልጽነት መፍጠር ይገባል" ብለዋል።
በዓለም አቀፉ የኤድስ ጤና ክብካቤ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ ገብረሚካኤል በበኩላቸው በኮቪድ-19 ክትባት ላይ ህብረተሰቡ እምነት እንዲያድርበት የክትባት ሂደቱን፣ ደህንነትና ግልጸኝነትን በተመለከተ በትብብር መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዳይሬክተሮቹ የወረርሽኙ የክትባት ሂደት ሰብአዊ ጉዳይ በመሆኑ ግልጸኝነት እንዲላበስ መንግስት በቅርበት መስራት እንዳለበት ጠቁመው፤ ድርጅታቸውም በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮቪድ-19 ክትባት የምርት ሂደት አስመልክቶ በህብረተሰቡና በሚመለከታቸው አካላት ላይ እምነት እንዲፈጠር ከተፈለገ በቅርበትና በትብብር መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ሲቪክ ማህበራቱ ከመንግስት ጎን በመሆን ማህበረሰባዊ የግንዛቤ ፈጠራና ሌሎች ሁሉን አቀፍ እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
የኮቪድ-19 ክትባት ማረጋገጫ ተሰጥቶት ወደ ተግባር ሲገባ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለአርብቶ እና አርሶ አደሩ በእኩል ደረጃ ተደራሽ እንዲሆን ከመንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።
መንግስት ለአገር በቀል እውቀቶች ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የኮቪድ-19 ጉዳይ ለአንድ ወገን እንደማይተው የተናገሩት ማህበራቱ፤ ሲቪክ ድርጅቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ማናቸውም አካል የወረርሽኙን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኮቪድ-19 ክትባት ማረጋገጫ ተሰጥቶት ወደ ተግባር እስኪገባ ህብረተሰቡ የቅድመ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም ማህበራቱ አሳስበዋል።
በቀጣይ 20 በመቶ የሚሆኑ አፍሪካዊያን የኮቪድ-19 የሙከራ ክትባት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ከሲቪክ ማህበራቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።