ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት አዲሱ የብር ኖቶች ቅያሬው ሊፈጥን እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት አዲሱ የብር ኖቶች ቅያሬው ሊፈጥን እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ
ባህር ዳር ፣ መስከረም 7/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ህገ ውጥ የገንዘብ ዝውውር እንቅስቃሴን ለመግታት አዲሶቹ የብር ኖቶች ቅያሬ በጥንቃቄ ፈጥኖ ሊከናወን እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁራን አሳሰቡ።
የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ምክትል ኃላፊና የምጣኔ ሃብት ምሁር ዶክተር ፀጋየ ጥበቡ ለኢዜአ እንዳሉት የብር ኖት ቅያሬው በሀገሪቱ የተፈጠረውን የኢኮኖሚና ፖለቲካ አለመረጋጋት ለማስተካከል ያግዛል።
ማህበረስቡ ሊቋቋመው በማይችልበት ሁኔታ የሸቀጦች ዋጋ እየናረ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው ብር በህገ-ወጦች ከባንክ ስርዓቱ ውጭ በጥቂት ግለሰቦች በመንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት 113 ቢሊዮን ብር ከባንክ ስርዓቱ ውጭ በግለሰቦችና ቡድኖች እጅ እንደሚገኝ ማስታወቁን አስታውሰዋል።
ይህም ጥቂት ህገ ወጥ ግለሰቦች እንደፈለጋቸው በመሆን የሸቀጦችን ዋጋ ንረትን እንዲያባብሱ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም አብሮ መኖርን የማይፈልጉ አካላት የእጅ አዙር ግጭቶችን እንዲያባብሱ ሰፊ አድል መፍጠሩንም አስረድተዋል።
ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ገንዘቡ እንዲመለስ በመንግስት በኩል የተሰጠው የሦስት ወር ጊዜ ግን እጅግ የረዘመ ነው ብለዋል።
በዚህ የተራዘመ ጊዜ ውስጥም ህገ- ወጦች ያስቀመጡትን ብር በተለያየ መንገድ ወደ ባንክ ስርዓቱ በማስገባት መልሰው ለተመሳሳይ ህገ ወጥ ዓላማ የሚያውሉበትን እድል እንደሚያመቻች አስረድተዋል።
ብሄራዊ ባንክ የጊዜውን ጉዳይ መልሶ በማጤን የብር ለውጡ በከፍተኛ ጥንቃቄና ፈጥኖ ማሰራጨት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአዲስ ብር ኖቶች ቅያሬም ከ45 እስከ 60 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ በቂ መሆኑንም ዶክተር ፀጋ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተጨማሪም መንግስት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ባንኮችን ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አመልክተዋል።
"የአዲስ ብር ኖቶችን ወደ ባንክ ለማስገባት የተሰጠው ጊዜ ረጅምና ለህገ-ወጦች አማራጭ ጊዜ የሰጠ ነው "ያሉት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ኤርሚያስ አሻግሬ ናቸው።
የተቀየሩት የ10፣ 50፣100 እና 200 ብር ኖቶች በፍጥነት ወደ ባንኮች እንዲሰራጭ በማድረግ መንግስት ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
የመቀየሪያ ጊዜውን ማሳጠር ካልተቻለ ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብ የኑሮ ውድነቱንና ግጭትን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የብር ኖቶች ቅያሬም የሃገሪቱን የኑሮ ውድነት፣ ሙስናን፣ የባንክ ብር እጥረትንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቅያሬ ጊዜው ግን መልሶ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዚህ በኋላ በሚደረገው የገንዘብ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ዝውውሩ ጤናማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።