ኅብረተሠቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ይበልጥ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኅብረተሠቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ይበልጥ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) ኅብረተሠቡ በሚያሳየው መዘናጋት ለኮቪድ -19 ወረርሽኝ ይበልጥ ተጋላጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ የዓለም ህሙማን ደህንነት ቀንን " የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ደህንነት ለህሙማን ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" በሚል መሪ ሐሳብ አክብሯል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዝቅተኛ እና በመካከለኛ የእድገት ደረጃ ላይ ያሉ አገራት በርካታ ዜጎቻቸው በጤና አገልግሎት ደህንነት መጓደል ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በእነዚህ አገራት ከአስር ህይወትን ከሚያሳጡ ምክንያቶች መካከል ከህክምና አገልግሎት ጥራትና ደህንነት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጥናትን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች ደህንነት ጉዳይ ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳና ሁለቱም ተነጣጥለው መታየት የሌለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ እስካሁን 1 ሺህ 429 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 1 ሺህ 200 የሚሆኑት ማገገማቸውን ጠቁመዋል።
የቀሩት በህክምና ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ኅብረተሠቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚቀርብለትን ምክረ-ሐሳብ በመቀበል አንድም ራሱን እንዲጠብቅ በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዲሆኑ ምክንያት መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ቡሬማ ሳምቦ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት "ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለጤና አገልግሎት ደህንነት ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል።
በተለይም ኮሮናቫይረስን በተመለከተ የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከመንግስት ጎን ሆኖ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ አሁን የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ በማጠናከር ምቹ የጤና አገልግሎት አካባቢን ለመፍጠር እንደሚሠራ ዶክተር ቡሬማ አረጋግጠዋል።
ቀኑን በማስመልከት በኮሮናቫይረስ ተይዘው በዘውዲቱ ሆስፒታል የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ህክምና የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ተጎብኝተዋል።