ቀጥታ፡

ታማኝ ግብር ከፋዮች በመንግስት ተቋማት ቅድሚያ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ ሰጡ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) ታማኝ ግብር ከፋዮች በመንግስት ተቋማት ቅድሚያ አገልግሎት እንዲሰጣቸው የሚያደርግ አሰራር እንዲዘረጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መመሪያ ሰጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ሁለተኛው ዙር የፌደራል ግብር ከፋዮች እውቅናና ሽልማት ዛሬ በተሰጠበት ወቅት ነው።

በስነ-ስርዓቱም 200 ግብር ከፋዮች በሶስት ደረጃዎች ተከፋፍለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም 20 ግብር ከፋዮች በፕላቲኒዬም ደረጃ፣ 60 ግብር ከፋዮች ደግሞ በወርቅ እንዲሁም 120 ግብር ከፋዮች በብር ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በዚህ ወቅት የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን የምትሆነው በመመኘት ሳይሆን ግብርን በአግባቡ በመክፈልና ገቢውንም በልማት ላይ በማዋል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የገቢዎች ሚኒስትር የአንድ መስኮት አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓቶችን እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2012 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 233 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

ገቢውም ከ2011 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ነው ያስረዱት።

በተለይ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የተሰበሰበው ገቢ በመልካም እንደሚታይም ተናግረዋል።

ግብራቸውን በታማኝነት የሚከፍሉ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ፤ ግብርን በመሰወርና በማጭበርበር ሀገርን የሚበዘብዙትም በርካቶች ናቸው ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

መንግስት የፈቀደውን ከቀረጥ ነጻ አገልግሎት እንዲሁም የወጪ ንግድ ማበረታቻ ላልተፈቀደ ጥቅም የሚያውሉና የሀሰተኛ ደረሰኝ የሚያሰራጩትን ለአብነት አንስተዋል።

"ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በህገ-ወጦች ላይ በተወሰደው እርምጃም መንግስት ሊያጣው የነበረን 27 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል" ብለዋል።

ከወሰድነው እርምጃ በህገ-ወጥ መስመር እየተንቀሳቀሱ ያሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበናልም ነው ያሉት።

የሀሰተኛ ደረሰኝን በማሰራጨትና በሀሰት አስመጭና ላኪ መስለው ደረሰኝ  ሲቆርጡ የነበሩ 223 ድርጅቶች ተለይተው መያዛቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ህግና ስርዓትን ብቸኛ መመዘኛ አድርጎ ለመስራት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው የዜጎች ኑሮ መሻሻል የሚችለው ታማኝ ግብር ከፋዮች ሲበራከቱ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም በመንግስት የአሰራር ውስጥ ታማኝ ግብር ከፋዮች ቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት እንዲዘረጋ መመሪያ ሰጥተዋል።

"ሌቦችን ማጥፋት ሳንችል ግብር መሰብሰብ ብቻውን ውጤት አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም መንግስት ሌብነትን ለማስቀረት ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

በተለይ በመንግስት ወገን ሆነው 'እጅ መንሻ' የሚጠይቁ ሌቦችን ለሚያጋልጡ ግብር ከፋዮች የግብር ቅነሳ የሚያደርግ አሰራር እንዲዘረጋም ነው ያሳሰቡት።

በመንግስት ባለስልጣናት ሽፋን ግብርን ለማጭበርበር የሚሞክሩ ባለሃብቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።

በዛሬው ስነ-ስርዓት በፕላቲኒዬም ደረጃ እውቅና ከተሰጣቸው 20 ኩባንያዎች መካከል ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሳሊኒ ኢፔርጄሎ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።   

የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊዮን ብር ከግብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም