አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ

72

መንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

የአዲስ ዓመት ወይም የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በየትኛውም አገር እንደየአገራቱ ታሪካዊ መነሻ፤ እንዲሁም ወግና ልማድ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድም ይህ በዓል የሚከበርበት ታሪካዊ ዳራ፣ ልማድና ወጋቻን ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ ትስስሮች የሚጠናከሩበት፤ ከግለሰብ ጀምሮ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ፣ በመንግስትና በተለያዩ አደረጃጀቶችም ጭምር አዳዲስ አስተሳሰቦችና ዕቅዶች ለመተግበር እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ወቅት ነው፡፡

አዲስ ዓመት የሁሉ ነገር መጀመሪያ፤ “ምንም ያልተጻፈበት ነጭ ወረቀት”፤ ዓመቱ አንድ ተብሎ የሚጀመርበት እንደመሆኑ መጠን፤ አዳዲስ አስተሳሰቦችም ጭምር የሚመነጩበትና የሚሰርፁበት ነው። ይህ ብቻም አይደለም አዲስ ዓመት የሚጀመርበት የመስከረም ወር ራሱ አዳዲስ ሁነቶችን የያዘና የዓመቱ መጀመሪያ ወራችንም ነው ለእኛ ለኢትዮዽውያን። አዲስ ዓመት ሲመጣ ኢትዮጵያውያን ከክረምቱ ዝናባማ፣ ብርዳማ አየር ተላቆ የመስከረም የተስፋ ብርሃን ከማየት ጀምሮ የሰማዩ ድምቀት እና የመልክዓ ምድሩ ልምላሜ እንዲሁም የአደይ አበባ ድምቀት ጋር ተደማምሮ ልዩ ደስታና ተስፋ ይሰጣል።  በአዲስ ዓመት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሕፃን አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይሉ በደስታ፣ በፍቅር ተሰባስበው “የእንኳን አደረሰህ አደረሰሽ “ መልካም ምኞት እየተለዋወጡ ያለፉትን ረስተው በአዲስ መንፈስ የወደፊቱን እያሰቡ አዲስ ተስፋ የሚሰንቁበት ነው።

አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስና በአዲስ ተስፋ ተቀብሎ ወደፊት ለመራመድ ሲታሰብ ያለፈው አሮጌው ዓመት ማስታወሱ አይቀሬ ይሆናል። በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት የተስተዋሉ  መልካም ተግባራትን በቀጣይነት አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ ባጋጠሙን ችግሮችና ፈተናዎች እንዲሁም ከተፈፀሙ ጥፋቶች ደግሞ ትምህርት ወስደን ወደፊት መመልከትና መራመድ የግድ ይላል።

ያለፈውን 2012 መለስ ብለን ስናስብ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው በዓመቱ በአንድ በኩል ወደፊት የሚያራምዱ ተስፋ ሰጪ ተግባራት የተከናወኑበት በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጡና ውስጣዊ ሰላም የሚነሱ፤ ስጋት የሚፈጥሩና እንደሀገርም ፈተና የደቀኑ በርካታ ተግዳሮቶችን አሳልፈናል። ዓመቱ ከምንጊዜው በተለየ ሁኔታ ከአእምሮ ሊጠፉ የማይችሉ ከባድና ተደራራቢ ፈተናዎች የተስተናገዱበት እንደነበር ብዙዎችን የሚያግባባ ነው።  በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ አለመረጋጋቶች፣ የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው ስጋትና ያስከተለው ቀውስ፣  የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም ከህዳሴው ግድብ ጋር ተያይዞ በዲፕሎማሲው መስክ የነበሩ ውጥረቶች ያለፈው ዓመት ትውስታችን ናቸው።

እነዚህ ችግሮች እና የተፈጠሩ የቀውስ ክስተቶች እንደስፋታቸውና ክብደታቸው መጠን ኢትዮዽያ እንደአገር የመቀጠል ህልውናዋ አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም  ይህን ክስተት በትኩረት ሲከታተለው እንደነበር ግልጽ ነው። በእርግጥም ለዘመናት አብሮን የቆየው ጠንካራ የአብሮነት፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበርና የመረዳዳት ዕሴቶቻችን ባያሻግሩን ኖሮ ሊሸረሽሩንና ሊያለያዩን የሚችሉ እንደነበሩ በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው። ለዘመናት ተሰናስሎና ተገንብቶ የቆየው ጠንካራ የአብሮነትና ማህበራዊ መስተጋብራችን በቀላሉ ሊበጠስ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የማይችል መሆኑንም ጭምር አስመስክሮ ያለፈ ሆኖ አልፏል። ይህን አብሮነት በቀላሉ እንዳይበጠስ ካስቻሉን ነባር ዕሴቶቻችን ባሻገር የዕሴቶቹ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማት እንዲሁም አባገዳዎች ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።

ያለፈው ዓመት በርካታ አስከፊ ሁነቶችን ያስተናገድንበት ቢሆንም በበጎ የሚነሱ ሁነቶች  የታዩበትም ነበር። ለአብነት ለመጥቀስ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድታታይ ያደረጋት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ሳተላይት ወደ ህዋ ያመጠቀችበት፣ ታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተከናወነበት፤ የቱሪዝም መስክ ሊያሳድጉ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱ በአዲስ አበባ የአንድነትና የወንድማማች ፓርኮች ግንባታ የተጠናቁበት ዓመት ነበር።  

እንግዲህ አዲስ ዓመት ሲታሰብ ቅድሚያ ትኩረት የሚስበው ከነበረው ውስብስብ ችግር ወጥቶ ወደ አዲስ ምእራፍ መሻገርን ነው። ስለሆነም ባሳለፍነው ዓመት የተስተዋሉ አሉታዊ ክስተቶች ዳግም እንዳናያቸው በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ በመሰነቅ እያንዳንዱ ሰው እንደዜጋ መወጣት ያለበት ሃላፊነት አለ ማለት ነው። ለዚህም ሁሉም በተሰማራበት መስክ እሴትን በሚጨምሩ ተግባራት ላይ ማተኮር፣ ለግጭትና ሁከት ከሚዳርጉ ጉዳዮች መራቅ፣ በማናቸውም አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለአገር ግንባታ በትጋት መስራት እና የመሳሰሉትን ሃላፊነቶች መወጣት ይጠበቅብናል። በኅብረተሰቡ መካከል የነበረው በጎ ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎለብት ማድረግም እጅግ አስፈላጊ ነው።

በአገራችን እንደተለመደው አዲስ ዓመት ሲመጣ የመስከረም የተስፋ ብርሃን ይዟቸው በሚመጡ ገጸበረከቶች ይጀምራል። በዚህች የአዲስ ዓመት መጀመሪያ በሆነችው መስከረም ወር ውስጥ ብቻ እንኳን፤ ሀገራችን በዩኔስኮ በዓለም በማይዳሰሱ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው በዓላት መካከል ሁለቱ ታላላቅ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት ወር ነው፡፡ እነርሱም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል እና በኦሮሞ ህዝቦች በድምቀት የሚከበርው የኢሬቻ በዓል ናቸው፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በዋናነት በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አዘጋጅነት የሚከበር ቢሆንም ይህ በዓል በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ማህበራዊ ትስስርን፣ የመረዳዳትንና የመደጋገፍ እሴትን በማጠናከር በኩል ጉልህ ድርሻ ያለው ነው። የኢሬቻ በዓልም አብሮነትን፣ መተጋገዝንና መከባበርን አጉልተው ሊያሳዩ የሚችሉ ሁነቶች የሚከወኑበት ነው። በጥቅሉ ገና በአዲስ ዓመት መጀመሪያ የህዝቦችን ወንድማማችነት፣ አብሮነት፣ መደጋገፍና መቀራረብን የማያጠናከሩ ሁነቶችን አክብረን እንደምንጀምረው ሁሉ ዓመቱን በሙሉ ይህን መሰል በጎ እሴቶች የሚያጎለብቱ በርካታ ሁነቶች ስላሉን በእንደዚህ መልካም ተግባራት ላይ ማሳለፍ የአዲስ ተስፋ ተጨባጭ መገለጫዎች ናቸው። 

ስለሆነም በአዲሱ ዓመት በግል፣ በማህበር፣ በድርጅቶች፣ በመንግስትና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ሊተገበሩ የታቀዱ ዕቅዶችና ትልሞች ሁሉ ውጤታማ እንዲሆኑ ልክ በዓላቱን በምናከብርበት የትብብር፣ የወንድማማችነትና የአብሮነት መንፈስ በጋራ በመቆም ስኬታማ ስራ ለመስራት መዘጋጀት ይጠበቅብናል። እንደሀገርም ይሁን እንደግለሰብ በአዲሱ ዓመት “ሩቅ ዓላሚ ቅርብ አዳሪ” እንዳንሆን በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ሰንቆ ለግል፣ ለወገንና ለሀገር አለኝታነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል። ሁላችንም በአዲስ መንፈስ በመነሳት ዓመቱ መልካም የምንሰማበት፣ የምናይበት፣ የምንተገብርበት፣ ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆ የቆየልንን የአብሮነት፣ የመተባበርና የመከባበር ዕሴት አጠናክረን የምናስቀጥልበት መሆን ይገባዋል። ይህን ለማድረግ ከእያንዳንዱ የልብ ቅንነት ይጠይቃልና በቅን ልቦና ወደ አዲስ ጎዳና ብለናል!

መልካም አዲስ ዓመት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም