በበጀት ዓመቱ ሁለት ወራት ለሕዳሴው ግድብ ከ272 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

83

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ272 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት ዜጎች ለሕዳሴው ግድብ በተለያዩ ጊዜያት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ሐምሌና ነሀሴ ወራትም ከ272 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ገንዘቡ የተገኘው በቦንድ፣ በስጦታ እና በ8100 አጭር የጽሁፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብሮች መሆኑንም ገልጸዋል።

"ባለፈው ነሐሴ ወር ከ152 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት ተችሏል" ብለዋል።

በሐምሌ ወርም ከ119 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ገቢ መሰብሰቡን አመልክተዋል።

በአጠቃላይ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ዲያስፖራው ባለፉት ሁለት ወራት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ1 ነጥብ 5  ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ 2004 ዓ.ም አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ ከ13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ከህብረተሰቡ መሰብሰቡን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ከተማ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ መሰብሰቡ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ወራት 213 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰበ ታቅዶ ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከሶማሌ ክልል መረከቡ ይታወሳል።

ከተማ አስተዳደሩ ዋንጫውን ከተረከበ በኋላ እስካሁን ድረስ በሦስት ክፍለ ከተሞች ዋንጫውን በማዞር ገቢ የማሰባሰብ ሥራ መስራቱን ነው አቶ ምስክር የገለጹት።

በእዚህም በአቃቂ ክፍለ ከተማ 80 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ አካላት ለመስጠት ቃል መገባቱን ተናግረዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማም 80 ሚሊዮን ብር ሲሰበሰብ፤ 26 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መገባቱን አመልክተዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ደግሞ 36 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ተጨማሪ 15 ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል መገባቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም የአራዳ ክፍለ ከተማ የህዳሴ ግድብ ዋንጫውን ከልደታ ክፍለ ከተማ ተረክቦ ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ነው።

አቶ ምስክር እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 789 ሚሊዮን ለማሰባሰብ አቅዷል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 80 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ የሚታወስ ነው።

የህዳሴው ግድብ ከተጀመረበት 2004 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

"የከተማው ነዋሪ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ መጓተት ጋር በተያያዘ የነበረው ተሳትፎ ተቀዛቅዞ እንደነበርና በግንባታው በተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች በታዩ ለውጦች ዳግም በነቃ ሁኔታ እየተሳተፈ ነው" ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ የውሃ ሙሌት ተከትሎ የህብረተሰቡ ተሳትፎ መጨመሩን የገለጹት አቶ ምስክር የመዲናው ነዋሪ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጠል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና የአራዳ ክፍለ ከተማ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ 30 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑ አስታውቋል ።

የክፍለ ከተማው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀሐዬ በኩረፅዮን በግድቡ ዋንጫ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ የአቀባባል ስነ ስርአት መስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

ዋንጫው እስከ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በክፍለ ከተማው እንደሚቆይ ጠቁመዋል።

ክፍለ ከተማው በ2013 ዓ.ም ሐምሌና ነሐሴ ወራት ብቻ ለግድቡ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዐቅዶ 26 ሚሊዮን ብር መሰበብሰቡን አመልክተዋል።

በክፍለ ከተማው የሚገኙ ባለሃብቶች 5 ሚሊዮን ብር ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውንም አቶ ፀሐዬ ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት ክፍለ ከተማው 70 ሚሊዮን ብር ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለመሰብሰብ አቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም