ቀጥታ፡

በክልሎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ በሰው ላይ የሞት አደጋ አለመድረሱ በመልካምነት የሚሰድ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በክልሎች ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ቢከሰትም በሰው ላይ የሞት አደጋ አለመድረሱ በመልካምነት እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
የፌደራልና የክልል አመራሮች በተለያዩ ክልሎች የተከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ ለመቋቋም መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተገኝተው ገምግመዋል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዳሉት በክልሎች ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢከሰትም ምንም ዓይነት የሞት አደጋ አለመድረሱ በመልካምነት የሚወሰድ ነው።

የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የጎርፍ አደጋው በተከሰተባቸው ሥፍራዎች በመገኘት አስፈላጊውን ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚከናወኑ እርዳታዎችን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ መቀመጡንም ዶክተር ዐቢይ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ በመነሳት የዜጎችን ሕይወትና ንብረት እየነጠቁ ያሉትን የጸጥታ እክሎች በተመለከተም ውይይት መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።

"በተለይም በድንበር አካባቢ የሚፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ በሚሹ ቡድኖች የሚቀናበሩ ናቸው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑትን ሁሉ በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚመራው ተልዕኮ እንደሚከናወንም ነው ያመለከቱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የታገቱት 29 ሰዎች እንዲለቀቁ ጥረት ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም