በወልቂጤ ከተማ 30 ተሽከርካሪዎች ለሩብ ክፍለ ዘመናት አገልግሎት ሳይሰጡ በቆሙበት ሳርና ዛፍ በቅሎባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በወልቂጤ ከተማ 30 ተሽከርካሪዎች ለሩብ ክፍለ ዘመናት አገልግሎት ሳይሰጡ በቆሙበት ሳርና ዛፍ በቅሎባቸዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2012(ኢዜአ) በወልቂጤ ከተማ ንብረትነታቸው የጉራጌ መንገዶች ሥራ ድርጅት የሆኑ 30 ተሽከርካሪዎች ለሩብ ክፍለ ዘመናት አገልግሎት ሳይሰጡ በቆሙበት ሳርና ዛፍ በቅሎባቸዋል።
የጉራጌ መንገዶች ሥራ ድርጅት የጉራጌን ህዝብ የመንገድና የትራንስፖርት እንዲሁም የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ መሰረቶች ለማሟላት በ1954 የተቋቋመ የህዝብ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በጉራጌ ተወላጆችና ቀናኢ አስተሳሰብ ባላቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ መዋጮ በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር /አሁን ጉራጌ ዞን/ በተለያዩ አካባቢዎች በጋና ክረምት ማገልግል የሚችል መንገድ ሰርቷል።
በወቅቱ ከወልቂጤ እስከ ሆሳዕና 126 ኪሎ ሜትር የሚረዝምና ሌሎች መንገዶች በድርጅቱ አባላት ወጭና በመንግስት የቴክኒክና የሰው ሃይል ድጋፍ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በዚህም መንገዶች ሲበላሹ በቀላሉ መጠገን እንዲቻል በሚል እሳቤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኮቴ ክፍያ አስጀምሯል።
የድርጅቱ 30ኛ ዓመት የመስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በ1985 ዓ.ም ለህትመት በበቃው መጽሄት ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው እስከ 1985 ዓ.ም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ 25 ተሽከርካሪዎች ነበሩት።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኤንትሪ አውቶቡስ፣ ቺንኳንታ 110 ኤ.ቲ፣ ሎንቺና 110፣ ሎንቺና 108፣ ላንድሮቨርና ቶዮታ 30 ተሽከርካሪዎች በወልቂጤ ከተማ በጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ጊቢ ውስጥ ሳር እና ዛፍ በቅሎባቸው ይገኛሉ።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብና ሥነ ሰብ ኮሌጅ መምህር ታኖ ገትር ለኢዜአ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ድርጅቱ እንዲዳከም ተደርጓል።
በዚህም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 30 ተሽከርካሪዎች በተለይ ከ1990ዎቹ በኋላ ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ተደርጓል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከዓለም ባንክ ብድር ስትጠይቅ የጉራጌ መንገድ ሥራ ድርጅት እንደማሳያ የምትጠቀምበት ትልቅ ፕሮጀክት እንደነበርም ገልጸዋል።
የጉራጌ ወጣቶች-ዘርማ/አርዲ ሊቀመንበር ወጣት ዳውድ ካሚል የጉራጌ ህዝብ መንገድ ይበልጥብኛል ብሎ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ በማዋጣት ባቋቋመው ድርጅት መጠቀም ቀርቶ የቆሙ ተሽከርካሪዎችን ማየት ያስቀጣ እንደነበር ገልጸዋል።
ለዓመታት ሰው እንዳያያቸው በቆርቆሮ ታጥረው የቆዩት ተሽከርካሪዎች ለእይታ የበቁት ከሁለት ዓመት ወዲህ ከመጣው ለውጥ በኋላ መሆኑን ይናገራል።
መምህር ታኖ እንደሚሉት የጉራጌ መንገዶች ሥራ ድርጅት የተቋቋመው ሀገር ወዳድ በሆኑ ዜጎች ሲሆን፤ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ሳይሰጡ ሳርና ዛፍ እንዲበቅልባቸው የተደረገው እነዚህን አካላትና ሌሎችን ለማዳከም የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ተሽከርካሪዎቹ ለረጅም ዓመታት ጸሀይና ዝናብ ተፈራርቆባቸው ከአገልግሎት ውጪ ቢሆኑም ሙዚዬም ተሰርቶላቸው እይታ ክፍት መሆን አለባቸው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለሃብቶች የጉራጌንና የኢትዮጵያን ህዝብ ቀደምት ስልጣኔና የትልልቅ ፕሮጀክቶች ባለቤትነት የሚያሳዩ በመሆናቸውን የሚያስታውስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያቋቁሙ ጠይቀዋል።
በድርጅቱ ተሽከርካሪዎች ላይ የተፈጸመው አሻጥር አሳዛኝ ነው ያሉት የወልቂጤ ከተማ የሰላም ሽማግሌዎች ሊቀ-መንበር አቶ ኢድሪስ መሀመድ፤ የሚመለከተው የመንግስት አካል በሀገር ሃብት ላይ የሚደርሰውን ውድመት አይተው አቅጣጫና መፈትሄ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት በመገኘት የዋና አስተዳዳሪውን ልዩ አማካሪና የጽህፈት ቤት ሃላፊ ሁለት የሥራ ሃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡት ቢጠይቅም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።