የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የብሄር ስም ይዘው መቋቋም እንደሌለባቸው ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የብሄር ስም ይዘው መቋቋም እንደሌለባቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ መስከረም 7/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የህዝብ ድምፅ ሆነው እንዲያገለግሉና የሰላምና መረጋጋት ምንጭ እንዲሆኑ የብሄር ስም ይዘው መቋቋም እንደሌለባቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ በብሄርና በሃይማኖት ሰበብ ግጭት የሚያባብሱ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በሚገባቸው ቁመና ላይ እንዲገኙ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ለሰዎች ሞትና ስደት እንዲሁም የንብረት ውድመት ግንባር ቀደሞቹ አባባሾች በብሄር ስም ተቋቁመው ከሙያው ስነ ምግባር ውጭ በወገንተኝነት የሚሰሩ የሚዲያ ተቋማት ናቸው ተብሏል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለኢዜአ እንዳለው፤ በኢትዮጵያ በብሄር ስም የተቋቋሙ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ውክልናቸው በእነሱ መጠሪያ ለተሰየመው ማህበረሰብ ብቻ አይደለም።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ አወቃቀርም ብሄርን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ብዙኃን መገናኛ ተቋማትም አፈጣጠራቸው የብሄር እንዲሆን አድርጎታል ብሏል።
ብዙኃን መገናኛ ተቋም ሲመሰረት ተገልጋዮቹ ሰው የሆኑ ፍጡራን ሁሉ እንጂ ለሆነ ቡድን ተብለው አይደለም ነው ያለው።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ የዜጎች በህይወት የመኖር በሰላም ወጥቶ መግባትና ሃብት የማፍራት መብት እንዲረጋገጥ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ከብሄር ስያሜ መውጣት አለባቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው ብዙ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከትግል ሚዲያነት ወጥተው ሙያው የሚጠይቀውን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር አክብረው ለመስራት ቃል ከገቡ በኋላ ከነበሩበት የባሰ ግጭት ቀስቃሽ ዘገባዎችን ሲሰሩ ታዝበናል ብለዋል።
በመሆኑም በተለይ በውጭ እያሉ ሙያውን አክብረው ለመስራት ቃል ገብተው ከመጡ በኋላ ተመልሰው ወደ ትግል የተቀየሩ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት አደብ እንዲገዙ አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም ግጭት ቀስቃሽ ለሆኑ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ላይ "ለምን" የሚል ጥያቄ ማቅረብ አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ የብዙኃን መገናኛ ታሪክ አንድም በመንግስት ተጽዕኖ፤ በሌላ በኩል በራሳቸው ድክመት ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማት መፍጠር እንዳልተቻለ ይነገራል።