የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ከፍታው ለመመለስ የባለ ድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ከፍታው ለመመለስ የባለ ድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው
ሐረር (ኢዜአ) መስከረም 7/2013 የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደ ከፍታው ለመመለስ የባለ ድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር አስገነዘቡ።
የጉብኚዎች ደህንነትና ሃይጂን ፕሮቶኮል በተግባር የተደገፈ ማሳያ መድረክ በሐረር ከተማ ተካሄደ።
በቱሪዝም ኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደው መድረክ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር የቱሪዝም ዲኤታዋ እንደተናገሩት በአለም አቀፍ ብሎም በአገራችን የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
ዘርፉን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስም የቱሪዝም ማገገሚያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት መዳረሻ ስፍራዎችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም በፈቀደ እገዛ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
“በዛሬው እለትም በሐረር ከተማ የተጀመረው ሞዴል የጎብኚዎች ፕሮቶኮል ማሳያ መርሃ ግብር ለነገው ስራ ተሞክሮ ስለሚሆን የዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር ይገባል” ብለዋል።
“የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ከፍታው ለመመለስ የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት፣ የግል ባለሀብቶች፣ የሙያ ማህበራት፣ ምሁራን ማህበረሰቡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦዋቸውን ማጎልበት ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው “የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተጽዕኖ በቱሪዝም ዘርፉ አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ እንዲታጣ አድርጓል”ብለዋል።
በተለይ በሆቴልና አስጎብኚ ድርጅት የተሰማሩትን ከባንክና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በማገናኘት ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ የማመቻቸት እንዲሁም በቱሪዝም ስራዎች ላይ የተሰማሩ አካላትን በተለይ በዶርዜ ጎጃምና አዳባ ዶዶላ ስፍራዎች ላይ የማበረታታት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅትም 53 በመቶ የሚሆኑ ያደጉ አገራት እንዲሁም 43 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ አገራት የቱሪዝም ስራቸውን ከፍተዋል”ያሉት ወይዘሮ ቡዜና ለዚህም የጎብኚዎችን ደህንነትና አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻላቸው መሆኑን ጠቅሰው ይህንን በመከተል የጉብኚዎች ደህንነትና ሃይጂን ፕሮቶኮል በተግባር የተደገፈ ማሳያ በሐረር ከተማ መጀመሩን ተናግረዋል።
“የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ሆቴሎች ገበያ በማጣት 83 በመቶ የሚሆኑ ተዘግተዋል ሌሎችም ተጎጂ ሆነዋል” ያሉት የኢትዮጵያ ሆቴሎች ገበያ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታሁን አለሙ ናቸው።
“እንደማህበሩም ሆቴሎችን በነጻ የኬሚካል ርጭት በነጻ እያካሄዱና ዘርፉን እያበረታቱ እንደሚገኙ ጠቁመው ይህም ስራ በሌሎች ከተሞችም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።
“የጉብኚዎች ደህንነትና ሃይጂን ፕሮቶኮል በተግባር የተደገፈ ማሳያ መጀመርም የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያገግም ያደርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
በአስጎብኚ ስራ የተሳተፈው ወጣት ሐይሉ ጋሻው በበኩሉ ኮቪድ 19 ባስከተለው ተጽዕኖ ለስድስት ወራት ስራ ማጣቱን እና በንባብና በተለየያዩ እንቅስቃሴዎች ራሱን በመጠበቅ ማሳለፉን ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት የጉብኚዎች ደህንነትና ሃይጂን ፕሮቶኮል በተግባር የተደገፈ ማሳያ ተስፋ እንደሰጠውና እርሱም አስፈላጊውን አስተዋጽኦ በማበርከት ዘርፉን ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚተጋ ተናግሯል።
በፕሮግራሙም ማጠቃለያ በሐረር ዱክ በር ላይ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚያገለግለው የአውቶማቲክ ዲስኢንፌክሽን ማሽን ተከላ ተካሂዷል´